እንኳን አደረሳችሁ!!
እንዴት ነው በዓሉ? ሞቅ ሞቅ ብሏል? ለነገሩ ምን ሞቅ ሞቅ አለ አሁንማ… እድሜ ለኮሮና ከቤተሰብ ፣ ከወዳጅ ዘመዶቻችንም ጋር ተገናኝተን እንዳናከብረው ፣ በእናት አጋፋሪነት … በእኛ ታዛዥነት እጅ የጣፈጠ ዶሮ ፣ በታላቅ ወንድም እጅ የተበለተ በግ ፣ በአባት ወይም በእናት ተባርኮ የተቆረሰ ድፎ ፣ ቡናው ፣ ጠላው ፣ ፈንዲሻው ፣ የበዓል ጫጫታው … እነዛ አሰልቺ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን ጨምሮ … አብረን እንዳንፈስከው ፣ አካላዊ ርቀትን አስገዳጅ አድርጎ መጣብን፡፡ በተለይ ላጤዎች!!!
ይሁን! የምንወዳቸውን ሁሉ እስከጠበቀልን ድረስ ፣ ለትንሽ ጊዜም ቢሆን ፣ ዶክተሮቻችን መፍትሔውን አግኝተው እስክንወጣው ድረስ … ለየብቻችን ፣ ተለያይተን እንቆያለን ፤ እንዲህ ዓይነት ታላላቅ በዓላትንም ለየብቻችን ለማክበር እንገደዳለን፡፡ ይህን ቀን ማለፋችን አይቀርምና፡፡
ከቤተሰብ ጋር በዓሉን ለማክበር አለመቻሌን ሳስብ ሳሰላስል ምን ትዝ አለኝ መሰላችሁ… “እሺ ቀድሞውኑም … ቤተሰቦቻችንን እየወደድን ፣ ከቤተሰቦቻችን ጋር በዓልን አብረን ማክበር እየፈለግን ፣ በነፃነት ከአባቶቻችን ጋር ጠላችንን እየጠጣን ፣ ለእናቶቻችን ቡና እያፈላን መዋል እየፈለግን ፣ ነገር ግን በዜግነታችን ምክንያት ስልክ ከመደወል የዘለለ ነገር ማድረግ የማንችል ስንት ነን?
የለመድነውን የልጅነታችንን የበዓል ግርግር የምንናፍቅ ፣ እንደማንኛውም አማኝ ቤተክርስቲያን ሄደን ጸሎት ቅዳሴያችንን ተካፍለን መመለስ የምንፈልግ ፣ ነገር ግን የተተከለብን የጥፋተኝነት ስሜት ልባችንን እና እግራችንን አስሮ ወደኋላ የሚጎትተን ስንት ነን?
ከቤተሰቦቻችን ጋር የተሻለ ግንኙነት ኖሮን በዓልን ለማክበር ተገኝተንስ ፣ ውሎአችን ሰቆቃ የሚሆንብን ስንት ነን? ዜግነታችን እንዳይታወቅብን በከፍተኛ ጥንቃቄ ስንንቀሳቀስ የበዓሉን ደስታ እና መልካም መንፈስ መካፈል የማንችልስ?
ይህንን ሁሉ ሳስብ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ጀምሮ ፣ በተለይም በማንነቴ ምክንያት ራሴን ከቤተሰቤ ማራቅ ከወሰንኩበት ጊዜ ጀምሮ እንዲህ ያሉ በዓላትን ከመረጥኳቸው አዳዲስ ቤተሰቦቼ ፣ ጓደኞቼ ፣ እኔን መሳይ ተገፊዎች ጋር እንዴት እንደምናሳልፍ ሳስታውስ እፅናናለሁ፡፡ ቤተሰብ ማለት እኔን በእኔነቴ የሚቀበለኝ እና የሚያከብረኝ ሰው እንደሆነ አምናለሁ፡፡ እርግጥ ነው ያለማወቅ እና የባህል እንዲሁም ኃይማኖት ተፅዕኖ የስጋ ቤተሰቦቻችን ማንነታችን ላይ ያላቸው ጥያቄ መንስዔ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ነገር ግን ከነሱ የማላገኘውን ዓይነት ፍቅር እና ድጋፍ በማንነቴ ላይ ጥያቄ ከሌላቸው የውዴታ ቤተሰቦቼ ፣ ጓደኞቼ ማግኘት እችላለሁና … እነሱን መረጥኩ፡፡ ያ ማለት ግን የስጋ ቤተሰቦቼን ሙሉ በሙሉ ከህይወቴ አስወጥቻቸዋለሁ ማለት አይደለም፡፡
እና… እንደኔ በእንደዚህ ዓይነት ኃሳብ የምትጋልቡ ካላችሁ …. አይዞአችሁ ብቻችሁን አይደላችሁም!
የስጋ ቤተሰቦቻችንን ሳንጠላ ፣ የራችንን የመረጥነውን ቤተሰብ መመስረት እንችላለን፡፡ ከስጋ ቤተሰቦቻችን ጋር በዓሉን ማሳለፍ ባንችል እንኳን ከጓደኞቻችን ፣ ከወዳጆቻችን ጋር አንድ የሚያደርገን ፣ በአንድ ጥላ ስር የሚሰበስበን ፣ በአንድነት የሚፈርጀን ማንነታችን ፣ እኛነታችን አለንና … ከመሳዮቻችን ጋር አብረን እንዋል! እንደጋገፍ ፣ እንበረታታ!!!
በዓሉን ከስጋ ቤተሰቦቻችን ጋር በፈቃድም ሆነ ተገደን ለምናሳልፍም .. ሦስት ነገሮችን አስታውሼ ነገሬን ላብቃ፡፡
ዜግነታችንን የሚያንኳስሱ ፣ የሚኮንኑ ወሬዎች (በተለይም ቤተሰቦቻችን ስለ ጾታዊ ተማርኮአችን የሚያውቁ ከሆነ) ፣ የ “መቼ ነው የምታገቢው/ባው?” ጥያቄዎች ፣ የአለባበስ እና የጸጉር አሰራር አስተያየቶች ፣ እንዲሁም ሌሎች ትዕግስታችንን ሊፈታተኑ የሚችሉ ነገሮች … ሊያጋጥሙን እንደሚችሉ ቀድመን አምነን ፣ ቀድመን መዘጋጀት አለብን፡፡ በራስ መተማመናችንን የሚነቀንቁ እና የጥፋተኝነት ስሜት ላይ የሚጥሉ ሁኔታዎች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ አምነን ራሳችንን ማሳመን እና መፍትሄዎችን ቀድመን ማዘጋጀት አለብን፡፡
በእንደዚህ ዓይነት ብዙ የቤተሰብ አባላት በሚሰበሰቡባቸው በዓላት ወቅት ከቤተሰባችን አባላት ጋር የምናሳልፈውን ጊዜ መጠን ፣ የምናወራባቸውን ርዕሶች ፣ የምንሳተፍባቸውን ክርክሮች እና አለመግባባቶች ወሰን እናበጅላቸው፡፡ መመከት ከምንችለው በላይ እንዲወረወርብን አንፍቀድ፡፡ በበዓላት ወቅት ከቤተሰቦቻችን ጋር የምናደርጋቸው አብዛኞቹ ነገሮች ማህበራዊ ፣ ባህላዊ እና ኃይማኖታዊ ስምምነቶች እና ግዴታዎች ናቸውና በእኛ ላይ የተጫኑ ፣ የግድ ማድረግ ያለብን ነገሮች ሆነው ሊሰሙን ይችላሉ። ነገር ግን የራሳችን ጠበቃ ራሳችን እስከሆንን ድረስ ከጊዜአችንም ከስሜታችንም ለነሱ መስጠት የሚገባንን ያህል ብቻ እንስጥ፡፡ እንወሰን፡፡ ነገሮች አስጨናቂ ደረጃ ላይ የሚደርሱ እና ከቁጥጥራችን ውጪ የሆኑ ከመሰለን ፣ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ወጣ እንበል ፣ ትንፋሻችንን በመሰብሰብ ራሳችን ላይ እናተኩር፡፡
ለራሳችንም ሆነ ለቤተሰቦቻችን እንራራ፡፡ ነገሮች የተስተካከሉ እንዲሆኑ ከመሻት እና ሳይስተካከሉ ሲቀሩ ቤተሰቦቻችንን ከመወንጀል ይልቅ ፣ ነገሮችን እንዳሉ በመቀበል ፍቅርን ባናገኝ እንኳን ፍቅርን እናሳይ ፤ በማህበራዊ ተፅዕኖ ውስጥ የተፈጠረ የተዛባ አስተሳሰብ እንጂ ሌላ ምንም እንዳልሆነ ለመረዳት እንሞክር፡፡ ይህም ለራሳችን አዕምሮአዊ ሰላም ስንል ነው፡፡
በሉ … በያላችሁበት መልካም ቀን ይሁንላችሁ! ከስጋም ሆነ ከፈቃድ ቤተሰቦቻችን ጋር የምናሳልፈው በዓል የፍቅር እና የመተሳሰብ እንዲሆን እመኛለሁ፡፡
ያለንን እያካፈልን ፣ አንዳችን ለሌላችን ቤተሰብ እንሁን!
ቸር እንዋል! የዜግነት ክብር