ሰላም ሰላም ቤተሰብ! እንዴት ከርማችኋል!?
የዚህ ቅዳሜ እንግዳዬ ድንቡሼ ገላ ወይም በቀድሞ ስሙ ስክሮል ዜር ይባላል፡፡ ለአብዛኛው የፌስቡክ ዜጋ ተጫዋች ፣ ቀልደኛ እና ተግባቢ ነው፡፡ ለአንዳንዶች ደሞ ….
ስለዚሁ ግልፅ እና ተጫዋች ባህሪው ፣ ነገሮችን ስለሚያይበት መንገዶች ፣ ስለ ህይወት ገጠመኞቹ ፣ ያለ ፈቃድ ስለመጋለጥ … ራሱን የተቀበለበት ሂደት … ስለ ቤተሰብ … ሌላም ሌላም ካለበት ሆኖ ቡናውን ፉት እያለ .. ተጨዋውተናል፡፡ ብዙ ብዙ ማውራት ብንፈልግም… ጊዜ ገድቦን ነበርና የቻልነውን ያህል ለመዳሰስ ሞክረናል፡፡
እነሆ!
ቤን፡ በመጀመሪያ የሥራ ጊዜህን ተሻምቼ እንዳወራህ ስለፈቀድክልኝ በዜጋው ስም አመሰግንሃለሁ፡፡
ድንቡሼ፡ ጊዜውስ ለዚህ ያልሆነ ለመቼ ሊሆን ነው፡፡ እኔም ስለጋበዝከኝ አመሰግናለሁ፡፡
ቤን፡ እሺ ድንቡሼ… ወይም በዱሮ ስምህ ስክሮል ዜር …. ልክ እንደ ባለፈው ሳምንት እንግዳዬ ናቲ አንተም መጀመሪያ ላይ ካገኘኋቸው ዜጎች ውስጥ አንዱ ነህ፡፡ እንዲያውም ከእነ ናቲ ጋር አንድ ቀን ነበር ያገኘሁህ፡፡ እና… አሁንም ድረስ ሳቂታ እና ደስ የሚል አቀባበልህ ትዝ ይለኛል፡፡ ከዛ በኋላም ሳውቅህ እንደዛው ነበርክ፡፡ ከሌሎች ሰዎችም ስላንተ ተጫዋች እና ተግባቢ ባህሪ ብዙ ብዙ ሰምቻለሁ፡፡ እንዴት ነው እንዲህ ዓይነት ተግባቦት ሊኖርህ የቻለው? እንዴትስ ነው ሁልጊዜ በሰዎች ፊት በጣም የተረጋጋህ ነገር ግን በጣም ቀልደኛና አስቂኝ ሆነህ የምትታየው?
ድንቡሼ፡ ባይዘዌይ የጀመርከው ፕሮጀክት ደስ ይላል፡፡
ቤን፡ አመሰግናለሁ፡፡ ግን ጥያቄዬን እኮ ጀምሬአለሁ፡፡ ሃሃሃ
ድንቡሼ፡ አይዞህ… ዛሬ ጊዜዬን ላንተ ነው የሰጠሁት፡፡ ቁጭ ብዬ ቡናዬን እየጠጣሁ እያወራሁህ ነው፡፡
ቤን፡ እኔም ካቲካላዬን ይዣለሁ፡፡ ሃሃሃ
ድንቡሼ፡ ይመችህ!
ቤን፡ እሺ! … መልሴን አሁን!
ድንቡሼ፡ ይመስለኛል ህይወትን ቀለል አድርጎ የማየት መርሆዬ ነው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ያለምንም ይሉኝታ ራሴን ለመሆን እና ያንን ሁላችንም የምንሻውን መልካም የሆነ ከባቢ ዓየር በቻልኩት መጠን መፍጠርን እንደ መመሪያ ስላነገብኩት ይመስለኛል፡፡
ቤን፡ ህምም… ህይወትን ቀለል አድርጎ ማየት እና ራስን ያለምንም ይሉኝታ እና መሳቀቅ መሆን … አብዛኞቻችን የሚጎድለን ቁልፍ ጥበብ እንደሆነ አምናለሁ፡፡
ቤን፡ ስክሮል ዜርን ላነሳብህ ነው፡፡
ድንቡሼ፡ ሃሃሃሃሃ….
ቤን፡ ብዙ ሰዎች… አንተ (ስክሮል ዜር) ፌስቡክ ላይ ትንሽ ሽብር ፈጣሪ ፣ ደፋር እና ብዙም ግድ የሌለህ እንደሆንክ ያስባሉ፡፡ እኔ ደግሞ በግሌ… እንደ ፌስቡክ ቅመም ነው የማይህ፡፡ ቀልዶችህ እና አንዳንድ ጊዜ የምታደርጋቸው ነገሮች ከምንኖርበት ፍርሃት ለደቂቃዎችም ቢሆን በሳቅ ኃይል ይለዩናልና፡፡ አንተ ግን ምን አስበህ ነው?
ድንቡሼ፡ ሃሃ … ብዙ ሰዎች … አዎ … ኖ ኖ… አንዳንዶች ጋር አዎ… ትንሽ ወጣ ያልኩ እመስላለሁ መሰለኝ፡፡ ነገር ግን ይህ ያልከው ባህሪዬ ወይም ተግባሬ በሚገርም ሁኔታ ከብዙ ሰዎች ጋር እንድግባባ እና እንድተዋወቅ … ብሎም ታሪኮቻቸውን ፣ ፍርሃቶቻቸውን ፣ ኃሳቦቻቸውን ፣ ምኞታቸውን ፣ ትግሎቻቸውን ፣ ተስፋቸውን … ሌላም ሌላም እንድጋራቸው አድርጎኛል፡፡ ሰዎች ያለምንም “ይገምተኝ ይሆን?” ፍራቻ እንዲቀርቡኝ አስችሎኛል፡፡ አስተውለህ ከሆነ ሰዎችን ወይም ማንነታቸውን በጭራሽ አልተናኮልም፡፡ ይልቁንም ቀለል ያሉ ጉዳዮች ላይ ነው ቀልዶቼን የምሰነዝረው፡፡ እናም ሰዎች እኔን እያዩ መድረስ የሚፈልጉበት የነፃነት ደረጃ ላይ መድረስ እንደሚችሉ ፣ ራሳቸውን ያለምንም ፍራቻ እና ይሉኝታ መሆን እንደሚችሉ አይተውበታል ብዬ አምናለሁ፡፡
እንዲህ እንድሆን ያነሳሳኝም ሰዎች ለፆታዊ ተማርኮአቸው (ሴክሹዋሊቲ) ያላቸው አረዳድ እና አመለካከት ቀለል እያለ ፣ ነፃ እየሆኑ ሲመጡ ማየት ይመስለኛል፡፡ ሁልጊዜም ኢምንት ከሆነው ፆታዊ ተማርኮአቸው በዘለለ ከሰውነት ማንነታቸው ጋር እንዲገናኙ መርዳት ፣ ዕውነተኛ ማንነታቸውን ሲሆኑ ማየት ደስ ይለኛል፡፡
ቤን፡ ድንቅ ነው፡፡ ግን…. አንተስ ምንድን ነበር የምታገኝበት? ምንድን ነበር ክፍያህ? የሰዎችን ሸክም መጋራቱ ስለሚያስደስትህ ብቻ ነው ወይስ ሰዎችን በዚህ መልኩ መርዳት በሆነ መልኩ አንተንም እያነፀህ እና እያስተማረህ ነበር?
ድንቡሼ፡ ቅድም እንዳልኩህ በዙሪያዬ ያሉ ሰዎች ሴክሹዋሊቲያቸውን ተከትሎ የሚመጡ ችግሮችን በቀላሉ ሲወጧቸው ማየት ነው…
ቤን፡ ቅድም “ ሰዎች ለፆታዊ ተማርኮአቸው (ሴክሹዋሊቲ) ያላቸው አረዳድ እና አመለካከት ቀለል እያለ ፣ ነፃ እየሆኑ ሲመጡ ማየት” ያልከው በጣም ተመችቶኛል፡፡ በሙሉ ማንነታችን ለመኖር ቁልፉ እንደሆነም አምናለሁ፡፡ ይበልጥ ከራሳችን ጋር ሰላምን በፈጠርን ቁጥር ፣ ህይወትን በቀላሉ እንደምንረዳት እና ችግሮቻችንንም በቀላሉ እየፈታን መሄድ የምንችልበትን ዘዴ እንደምናዳብር ስለማምን፡፡
ድንቡሼ፡ ዕውነት ነው! ምን አስታውሳለሁ መሰለህ …. ሰዎች መጀመሪያ ላይ ስለራሳቸው ሲያወሩኝ … እንዴት ተስፋ እንደቆረጡ ምናምን ነበር የሚነግሩኝ፡፡ ከዛ ግን ብዙ ብዙ ስናወራ … አብዛኛውን ጊዜ ወደራሳቸው ተመልሰው ፣ ለራሳቸው ቅድሚያ ለመስጠት ወስነው ደስ ሲላቸው አያለሁ፡፡
ግን ደግሞ አንዳንዶችም አሉ … ህይወትን ለመረዳት ከበድ የሚላቸው፡፡ እነሱን ምንም አልላቸውም ነበር … በቃ… በቻልኩት እሞክራለሁ… ካልሆነ …አልሆነም ነው፡፡ አሁን ግን ወደኋላ መለስ ብዬ ሳየው … ምናልባትም ሌሎች ነገሮችን መሞከር እችል ነበረ… ብዬ አስባለሁ፡፡
ቤን፡ እንግዲህ የሚቻለውን ነው፡፡
ቤን፡ ያው እንደምታውቀው … አሁን ላይ ባሉት እንቅስቃሴዎች ይህንን እንዴት ማስቀጠል ይቻላል ብለህ ታስባለህ? የተሻለ አካላዊም ሆነ አዕምሮአዊ ጤና ያለው የዜጋ ማህበረሰብ ለመፍጠር ምን መደረግ አለበት ትላለህ?
ድንቡሼ፡ ዕውነት ለመናገር አሁን ላይ መደረግ ያለባቸውን ነገሮች ማማረጥ የምንችልበት ሁኔታ ላይ ያለን አይመስለኝም፡፡ መደረግ ያለበት ሁሉ ተደርጎ ደህንነታችን መረጋገጥ አለበት፡፡ የሁሉም ግብዓት በእኩል ሁኔታ አስፈላጊ ነው፡፡ ምናልባት ግን የሚስማማንን መርጠን እዛ ላይ መሳተፍ ወይም የተቻለንን አስተዋፅዖ ልናደርግ እንችል ይሆናል፡፡
ሮቤል ራሱን አውጥቶ ኢትዮጵያ ውስጥም ዜጋ እንዳለ አሳይቶ በዓለም አቀፍ ደረጃ አስተዋውቆናል አስተዋውቆናል፡፡ እነ ኩቺ ደግሞ በአለን ፖድካስታቸው ፣ እነ ናቲ ፣ አዲስ አሊያንስ እና 1ዜጋ ደግሞ በጤናው ዘርፍ ንቃትን ለመፍጠር እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡
በተለይም ቀደምቶቹ ዜጎች ፣ እነ አጠለል ፣ ብርጣሉ ፣ አዚዛ እና ሌሎችም ከስንቱ ጋር በመታገል ፣ ስንት ዱላ እና ስድብ እየደረሰባቸው አሁን የምናውቃቸውን ፣ ዜጋው በህብረት የገናኝባቸውን እና የሚዝናናባቸውን ቦታዎች ለማግኘት ጥረዋል፡፡ ውለታቸውም አለብን፡፡ ኢንተርኔት ከመምጣቱ በፊት ዜጎች የሚገናኙባቸውን ዘዴዎች በመፍጠሩ ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል፡፡ አሁን ላይ ሰው ስንተዋወቅ “ ፌስቡክ ላይ እንዴት መጣህ “ ምናምን ነው የምንባባለው ፣ ያኔ ግን እዚህ ቦታ ላይ ማን አመጣህ … ይኼን ቦታ እንዴት አወቅኸው … ነበር የምትባለው፡፡ የግንኙነት መንገዶች ትንሽ እና ጠባብ ቢሆኑም ፣ አሁን ኦንላይን ያለውን ያህል ፣ ትውውቁ እና ግንኙነቱ መሬት ላይም ነበር፡፡ ያኔ ነው የዜጋው ግንኙነት እና ህብረት የጀመረው ብዬ አምናለሁ፡፡
እነ ኦርዲናሪ ዛክ ደግሞ በስነፅሁፉ (በህትመት ዘርፍ) የራሳችን ውክልና እንዲኖረን ብዙ ለፍተዋል ፣ እየለፉም ነው፡፡
እና የሁሉም ተሳትፎ በእኩል ደረጃ አስፈላጊ ነው፡፡ በእኩል ደረጃ ለዜጋው ጠቃሚ ነው፡፡ ማበላለጥ አንችልም፡፡ ሁሉም በየመስኩ ፣ በየዘርፉ የቻለውን ያድርግ፡፡
ስለዚህ ይህንን ነው የማስበው … ወይም መሆን እንዳለበት የማምነው፡፡ ሁላችንም ለአንድ አላማ እስከቆምን ድረስ የእያንዳንዱን ሰው ጥረት/አስተዋፅዖ ማድነቅ ፣ መገንዘብ እና ሌሎች ብዙ ጀግኖችን መፍጠር ፤ ወይም እንዲፈጠሩ መንገዱን መክፈት፡፡
ታናናሾች እያዩአቸው ሊበረታቱባቸው ፣ አርአያ ሊያደርጓቸው የሚችሉ ጀግኖችን መፍጠር ይኖርብናል፡፡
በትክክል የሚወክሉን ሰዎች ያስፈልጉናል፡፡ ምን ታስባለህ?
ቤን፡ ምን አስባለሁ? እኔ? ሃሃሃሃ… ነገሮችን የምታይበት መንገድ ገርሞኛል፡፡ የሆነ ሌክቸር አዘጋጅተን እንጋብዝህ ይሆን?
ድንቡሼ፡ ሃሃሃሃ… ለምን አይሆንም? ግን ታዳሚውን አስበው … ሃሃሃሃ
ቤን፡ እኮ!
ድንቡሼ፡ የምር ግን ይሄ አንተ የጀመርከው ስራ እንዲህ እንዲሆን ነው ምኞቴ… የምንማማርበት፡፡ “አለን” የሚለው ፖድካስት ትዝ ይልሃል? በእነ ኩቺ የተጀመረው?
ቤን፡ አዎ! በደንብ
ድንቡሼ፡ በጣም የሚገርም ድንቅ ሃሳብ ነው፡፡ እንደዛ ዓይነት . በተለይም ትኩረታቸው በአብዛኛው መሬት ላይ ባለው የዜጋው ማህበረሰብ ዕውነተኛ የኑሮ ሁኔታ ላይ የሆነ ፣ ዜጋው ስለሚኖረው ህይወት የሚዳስሱ ፣ የዜጋውን ስነ ልቦና የሚያንፁ የተለያዩ መድረኮች ያስፈልጉናል፡፡
ቤን፡ እንዲያውም … እርግጠኛ ነኝ ይሄንን ጨዋታችንን ማንበባቸው አይቀርም፡፡ ለሚሰሩት ስራ ጥሩ ጥቆማ ሊሆን ይችላል እና ሌላም የምትለው ካለህ…
ድንቡሼ፡ ጅምራቸው አሪፍ ነው፡፡ ነገር ግን ያ ዲያቆን ደረጄ ለሚለፈልፈው ትርኪሚርኪ መልስ መስጠታቸው እንዳለ ሆኖ ሀገር ውስጥ ስላለው ኢትዮጵያዊ የዜጋ ህይወት … ስለ ጨዋታው ፣ ስለ ቀልዶቻችን ፣ እንዴት እንደምንግባባ ፣ እንዴት አብረን ጊዜ እንደምናሳልፍ … ሰው ሰው የሚሸት… አለባበሳችን ፣ ፋሽናችን ሌላም ሌላም ቢጨምሩበት አሪፍ ነው፡፡ የሚደርስብንን መገለል እና መድልዎ እንዴት በቀልድ መልክ እንደምናፈራርሰው .. እንደምናልፈው … የመግባቢያ ቋንቋዎቻችን… ሌላም ሌላም … ቀለል ባለ ሁኔታ መሬት ላይ ያለውን ህይወት ቢያሳዩበት አሪፍ ነው፡፡
በተለያየ ዘርፍ ስኬታማ የሆነ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ምን ይመስላል? ሰዎች ዜግነታቸውን ከሌላው ከሰፊው ማህበረሰብ ጋር ካላቸው ህይወት ጋር አመጣጥነው እንዴት እንደሚኖሩ… በተለያየ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ዜጎች ያላቸው ራስን የመግለጥ (ካሚንግ አውት) ሂደት …. ሰዎች “ጌይ” ወይም “ዜጋ” ከሚሉት ቃላት ወይም ስያሜዎች ጋር እንዴት ተዋወቁ? … የዜጋ ቋንቋችንስ እንዴት እያደገ ነው?… ብዙ ብዙ ነገር ማካተት ይቻላል፡፡ እንዲህ ያሉ ፕሮግራሞች መጀመሪያ ላይ ስለዜጋው ለዜጋው መሆን አለባቸው የሚል የግል አስተያየት አለኝ፡፡
በተጨማሪም ደግሞ … ቁምነገር የሆኑ ነገሮችን፣ ለምሳሌ እኩል የሆነ የጤና አገልግሎት ለአንድ ከሴክሹዋሊቲው ጋር ለሚታገል ሰው ምን ማለት እንደሆነ በደንብ ማሳየትም ይቻላል፡፡
ቤን፡ በአለን ስም አመሰግናለሁ … ማለት የምችል ይመስለኛል፡፡ ሃሃሃ
የምር ግን…. እዚህ ሀገር ውስጥ ያለው የዜጋ ባህላችን ዕድገት እና የራሱን የሆነ ቅርፅ እየያዘ ፣ ከተለያየ የዜጋው ማህበረሰብ ክፍል ውክልና እያገኘ መምጣቱ እንዴት ያስደንቀኛል መሰለህ፡፡ አንተ እዚህ እያለህ እንዴት ነበር? ጨዋታው … ምናምን ምን ይመስል ነበር?
ድንቡሼ፡ ሃሃ… በ90ዎቹ አካባቢ (98 በትክክል) ከዜጋው ማህበረሰብ ጋር እንደመተዋወቄ እና ከእኔ በፊት የነበሩ ዜጎችን ለማግኘት እና ለመግባባት ኢንተርኔት ብቻ እንደነበረው አንድ ዜጋ ስናገር … ያኔ ጨዋታ ፣ ሳቅ እና ቀልዶች ነበሩ የዘመናችን የመግባቢያ እና የአብሮነት መሠረቶቻችን፡፡ ትዝ ይለኛል…. ጓደኞቼ ነበሩ የመጀመሪያዎቹን ፓርቲዎች… ያለ መግቢያ ክፍያ በነፃ ያዘጋጁ የነበሩት፡፡ ከዛም ክፍያ ምናምን ተጀመሮ ለማየት በቃን፡፡
ቤን፡ ስለ “ላባ ግሩፕ” ነው እያወራኸኝ ያለኸው?
ድንቡሼ፡ ኖ ኖ… ከላባ በፊት ነው እንጂ …. አሪያ እና ቤላ ነበሩ የሚያዘጋጁት፡፡ ምሽቱን በሙሉ… ነፃ ነበር… ዜጋው ተሰብስቦ እንዲዝናና እና እንዲጫወት ብቻ… አራት ወይም አምስት ጊዜ ተዘጋጅቶ ነበር
ቤን፡ ከላባ በፊት? እንዴ… ስንት ዓመትህ ነው? ሃሃ
ድንቡሼ፡ ሃሃሃሃሃ….35 ሆኖኛል
ቤን፡ ሃሃሃ… ኧረ መመለስ አይጠበቅብህም ነበር ይሄን ጥያቄ፡፡ ለነገሩ በሁለት ብቻ ነው የምትበልጠኝ፡፡ ወይኔ!!!… እያረጀን ነው!!!
ድንቡሼ፡ ግን ልክ እንደ ወይን እየጣፈጥን!
ቤን፡ ሃሃ… ዕውነት ነው!
ድንቡሼ፡ እና ጥያቄዎችህን መለስኩልህ?
ቤን፡ አዎ! በደንብ… ግን ሌላም አለኝ
ድንቡሼ፡ እሺ
ቤን፡ እንዴት ነበር ራስህን ያወቅኸው? ብዙም ስለዜግነት በማይወራበት ማህበረሰብ ውስጥ … ዜጋ መሆንህን እንዴት አወቅህ? እንዴትስ ተቀበልከው?
ድንቡሼ፡ ዜጋ (ጌይ) መሆኔን የተረዳሁት ወይም ያወቅሁት በሁለት መንገዶች ነው፡፡ የመጀመሪያው፡ ክፉ ደግ መለየት ከጀመርኩበት… ከ3 ዓመቴ ወይም ከዛ በፊት አካባቢ ጀምሮ የነበረኝ ሁናቴ ነው ፣ የማሳየው ባህሪ … ከእህት ወንድሞችህ ፣ ከአብሮ አደጎችህ ጋር ስትጫወት ከፆታ አቻዎችህ ተቃራኒ የምታደርጋቸው ነገሮች ምናምን ማለት ነው፡፡ ዕቃ ዕቃ ስትጫወት ሙሽራ ሆነህ ሻርፕ ወይም ነጠላ እንደ ቬሎ መልበስ ፈልገህ ስትከለከል … እጆችህን አጣምረህ ፣ ትንሽዬ ለንቦጭህን ጥለህ ፣ ትንንሽ ዓይኖችህን እያቁለጨለጭክ የምታኮርፈው ነገር….
ከዛን ጊዜ ጀምሮ ነበር የተለየሁ መሆኔን ያወቅሁት፡፡
ሁለተኛው ደግሞ፡ ሃይስኩል እያለሁ …13 ዓመቴ አካባቢ ጌይ የሚለው መጠሪያ ወይም ቃል የፆታዊ ተማርኮ መጠሪያ መሆኑን እና እኔ ከሚሰማኝ ስሜት ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ያወቅሁ ጊዜ ነበር፡፡ በጣም አስደንግጦኝ ነበር፤ ዓለም ላይ እኔ ብቻ ያለሁ እስኪመስለኝ ድረስ እፍረት ፣ ፍርሃት ፣ ልዩነት (መነጠል) ተሰምቶኝ ነበር፡፡ ይባስ ብሎም ቤተክርስቲያን እየተቃወሙት የሚሰብኩትን ሰይጣን ሁሉ የሆንኩ መስሎኝ ነበር፡፡
ቤን፡ ይህን ሁሉ መጥፎ ስሜት እንዴት ከራስህ ላይ አውርደህ ጥለህ አሁን ያለህበት ራስህን የመውደድ ደረጃ ላይ እንዴት ደረስክ ታዲያ?
ድንቡሼ፡ ከራሴ ጋር ሰላም እንድፈጥር እና ወደራሴ እንድመለስ የረዳችኝ እናቴ ናት፡፡ ምንም ነገር ቢገጥመን ፣ ምንም ነገር ብንጋፈጥ በማንበብ እና ራሳችንን በዕውቀት በማነፅ ልንፈታው እንደምንችል ሁልጊዜ ትነግረን ነበር፡፡ ሃይስኩል እያለሁ የነበረኝ የማወቅ ጉጉት ጉዳዩ በሌሎች ሃገራት ፣ በተለይም ባደጉት ሃገራት የተለመደ እንደሆነ እና እና ሀገር ግን ነውር እና ሃጢያት ተደርጎ እንደሚቆጠር አስተማረኝ፡፡ ኮሌጅ ከገባሁ በኋላ ደግሞ ኢንተርኔት የተመሳሳይ ፆታ ፍቅር ሰውኛ እንደሆነ እና እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥም የተለየ እንዳልሆነ አስረዳኝ፡፡
ራሴን ሙሉ ለሙሉ እንድቀበለው የረዳኝ ደግሞ እንዳልኩህ አስተዳደጌ ነው፤ ለራሴ ዕውነተኛ ስሜት ታማኝ እንድሆን ፣ ራሴን እንዳከብር ፣ ለራሴ እንድቆም ፣ ምንም ነገር እንዳልፈራ ሁልጊዜም እበረታታ ነበር፡፡ ስለዚህ… ሌሎች ነገሮች ላይ ከመምጣቴ በፊት ሙሉ በሙሉ ጌይ መሆኔን አውቄ ፣ የማንም ጉዳይ እንዳልሆነ አምኜ … ራሴን 101% ሆኜ አለሁ እልሃለሁ፡፡
ቤን፡ ግሩም ነው! ኃይማኖትስ…
ድንቡሼ፡ ኃይማኖት…. ለእኔ ራስህን የምትገድብበት ሳጥን ነው፡፡ መንፈሳዊነት ደግሞ ራስህን ከአካባቢህ ጋር አስማምተህ ለተሻለ ነገር ፣ ለታላቅ ኃይል የምትንቀሳቀስበት ጌጥህ ነው፡፡ መንፈሳዊ ሰው ነኝ፡፡ በገነትም ይሁን እዚሁ ምድር ላይ ፣ ራሱ ሰው ቢሆንም ፣ በፀሎትም አግኘው በምን ወይም በተመስጦ ፣ ወይም በሌላ ዕምነታዊ ሥርዓት ፣ ምርጡ ማንነታችን ፣ እኛነታችን ላይ እስካደረሰን ድረስ ፣ “ፈጣሪ” የሚለውን ሃሳብ እወደዋለሁ፡፡ በቃ ደስ ይለኛል፡፡
ቤን፡ አሁን ደግሞ ድንቅ ነው! ሃሃሃ … ትርጉም የሚሰጥ ነገር ነው እየነገርከኝ ያለኸው እና…አመሰግናለሁ፡፡
ቤን፡ ማንነትን … ወይም ዜግነትን ለሌሎች ስለማሳወቅ (Coming Out) እናውራ እስቲ ፡፡ ለቤተሰቦችህ አባላት ተናግረህ ታውቃለህ? ካወቅህስ ከነሱ ጋር ያለህን ግንኙነት ምን ዓይነት አድርጎታል?
ድንቡሼ፡ ለቤተሰቤ አልወጣሁም … ግን ብነግራቸውም ብዙም የሚደነቁ አይመስለኝም፡፡ የቅርብ ጓደኞቼ ግን ያውቃሉ፡፡ የኮሌጅ ጓደኞቼም… ሁሉም ማለት ይቻላል ያውቃሉ፡፡
ቤን፡ እንዴት ነው ግንኙነታችሁ? … ከቤተሰብህ ጋር ማለቴ ነው
ድንቡሼ፡ በጣም አሪፍ ነው፡፡ የደስታቸው ማዕከል እኮ ነኝ… ምን ትጠብቃለህ ሌላ? በጣም ነው የምወዳቸው ፣ የማከብራቸው፡፡ እናቴ ብዙም ላትገረም ትችላለች – ብነግራት፡፡ ወንድም እህቶቼ ግን… እኔንጃ! የሚደነግጡ ግን አይመስለኝም፡፡ አንዳንዴ የትዳር ወሬ ምናምን ሲነሳ “በናንተ ህይወት ጣልቃ እንደማልገባው ሁሉ ፣ እናንተም እንደዛ እንድትሆኑ እፈልጋለሁ” ብዬ መንገዱን እዘጋባቸዋለሁ፡፡ ስለዚህ ያን ያህልም ጫናው አይሰማኝም፡፡
ቤን፡ ሳትፈልግ ተናግረህ… ወይም ተገደህ… ወይም ሌሎች ሰዎች ያላንተ ፈቃድ እና ዕውቅና አጋልጠውህስ ያውቃሉ?
ድንቡሼ፡ እንዴ… አዎ! በፊት የምሰራበት መስሪያ ቤት የሆነ ጊዜ በሙሉ አውቀው ነበር፡፡
ቤን፡ የምህርህን ነው? እና ምን ተፈጠረ?
ድንቡሼ፡ የመጀመሪያ ቦይፍሬንዴ ነበር ያደረገው፡፡ ሚስት እንዳለችው ሳውቅ እሸሸው ጀመር፡፡ በጣም ተናዶ ስለነበር ሊበቀለኝ የፈለገው ደብዳቤ በመፃፍ ነበር… ለኔ፡፡ ከዛ… ደብዳቤውን ለኮሌጅ ጓደኞቼ ላከው፡፡ እነሱም እኔን ለማብሸቅ እና ለመሳደብ ምክንያት ነበር የሚፈልጉት፡፡ እናም ይሄን እሱ የላከውን ደብዳቤ መጀመሪያ ካነበቡት በኋላ የመስሪያቤታችን ካፌ መግቢያ ላይ… ሁሉም ሰው እንዲያነበው ብለው ለጠፉት፡፡
በኋላ ላይ ሁለት ሴቶች መጥተው ለኔ የተላከ ደብዳቤ እንደተለጠፈ እና ሄጄ እንዳነሳው ነገሩኝ፡፡ ሄጄ ባነሳውም… ግን ሁሉም ሰው ቀድሞ አንብቦት ነበር፡፡
ያሳይህ እንግዲህ…. እንደዛ ነው የወጣሁት!
ቤን፡ ዋው! በእርግጠኝነት አስፈሪ እና አስደንጋጭ ነገር ነበር፡፡ ከዛ በኋላስ? ሥራ…
ድንቡሼ፡ ቢሮአችን አንድ ዝም ብሎ የሚከታተለኝ ነገረኛ ሰው ነበር፡፡ ኮምፒውተሬን ከፍቶ ያየኋቸውን ፣ የማያቸውን ፣ ያለሁባቸውን ዌብሳይቶች በሙሉ እያወጣ ለቢሮው ሰው በሙሉ አሳየብኝ፡፡ Adam4Adam, Romeo.. እና ሌሎችም አሁን የረሳኋቸው ገፆች ነበሩ፡፡ ለዲፓርትመንታችን ሰው በሙሉ አሳያቸው… ይባስ ብሎ ኮምፒውተሬ ውስጥ የነበሩ የተወሰኑ ወጣ ያሉ ፎቶዎች ፕሪንት አድርጎ ሁሉ አወጣቸው፡፡ ከዛ አለቃችን ጠርቶ ሲጠይቀኝ … ራሴን በመፈለግ እና በማወቅ ሂደት ውስጥ እንደሆንኩ እና ማንም ምንም እንደማያገባው … ኮምፒውተሬንም የመክፈት ምንም መብት እንደሌለው ቀጥ ብዬ ነገርኩት፡፡
ሁለቱም አሳዛኝ ታሪኮች ናቸው ብዬ አላምንም፡፡ በራሴ ዕምነት አለኝ ፤ እንዲሳለቁብኝ አልፈቀድኩላቸውም … እንዲያውም የበለጠ ራሴን እንዳውቅ ፣ እንዳነብ ፣ የበለጠ ራሴን እንድሆን ጥንካሬን ሰጥቶኛል፡፡ ከዛ በነጋታው ይውጣላችሁ ብዬ ነፍሷን ይማረውና ዳኒ አይዶል የሰራችልኝ ልብስ ነበር… ግማሽ ራቁቴን ሆኜ ቢሮ ሄድኩ፡፡ ሃሃሃሃሃ
ቤን፡ ዳኒ በጣም ጎበዝ ነበር፡፡ ነፍሱ በሰላም ትረፍ፡፡
ድንቡሼ፡ በጣም! አሜን!
ቤን፡ እሺ ድንቡሽዬ …. ጥያቄዎቼ የሚያልቁ ባይሆኑም… በእርግጠኝነት ሌላ ጊዜ ተገናኝተን ሌሎች ጉዳዮች ላይ እንቀድዳለን ብዬ አምናለሁ፡፡ ለዛሬ በዚህ ይብቃን? ካቲካላውም ሰራ መሰለኝ፡፡
ድንቡሼ፡ አመሰግናለሁ ቅመሟ! እናወራለን በደንብ… ያቺ ዶንኪ ቂጥህን በደንብ ተንከባከባት! ሃሃሃሃ