COVID-19: ወሲባዊ ግንኙነትእና ሊደረጉ የሚገባቸው ጥንቃቄዎች

ጤና ይስጥልን ዜጎች!

እንዴት ናችሁ?

ምነው ሰሞኑን ወሲብ ወሲብ አልክብን እንደምትሉኝ …. ቢሆንም ግን የህይወታችንን ፣ የኑሮአችንን ሁኔታ የምናውቀው ነውና ፣ ያገኘሁትን ሁሉ መረጃ ለማካፈል ስለፈለግሁ … እነሆ!

ሁላችንም እንደምናውቀው ወቅቱ COVID-19 ዓለምን እያነጋገረ ያለበት ፣ የሰው ልጅ ተፈጥሮአዊ ባህሪይ የሆነውን ማህበራዊ መስተጋብር እየተገዳደረ ፣ ታላላቅ ኢኮኖሚዎችን እየናደ እና አቅም እያሳጣ የሚገኝበት ፣ የሰዎች የዕለት ተዕለት ኑሮአቸውን እያስተጓጎለ በአንድ ቦታ ብቻ ተወስነው እንዲቀመጡ እያስገደደ ያለበት ፣ አለዚያ ግን በፍጥነት በመዛመት ምን ያህል ገዳይ እንደሆነ ያረጋገጠበት … ለሰው ልጅ ክፉ የሆነ ወቅት ነው፡፡

ታዲያ በዚህ ባለንበት ጊዜ ሰዎች ወረርሽኙን ለመከላከል የተለየያዩ መፍትሄዎችን እንዲጠቀሙ የዓለም መንግስታት ፣ በተለይም የዓለም የጤና ድርጅት መመሪያዎችን ቢያስቀምጡም … የመከላከል አስተማማኝነቱ በደንብ የተሰመረበት መንገድ ግን “አካላዊ ፈቀቅታ ነው”፡፡ እንኳን ከሌላ ሰው ጋር መገናኘት ቀርቶ … የራስን እጆች እንኳን ሳናምን በየጊዜው በሳሙና በደንብ በመታጠብ ፣ እንዲሁም በአልኮል እና ሳኒታይዘር እንድናፀዳ እየተመከርን ያለንበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡

የሰው ልጅ ግን ተፈጥሮአዊ የሆነውን የማህበራዊ መስተጋብር ፍላጎቱን እና ባህሪውን እንዴት መተው ይቻለዋል? በተለይም እንደ አፍሪካ ባሉ በኢኮኖሚያቸው ዝቅተኛ የሆኑ ህዝቦች ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮአቸውን የግድ ከሌሎች ጋር ባላቸው ግንኙነት መሰረት ያደረጉ ፣ እንዴት ሁሉን ነገር ርግፍ አድርገው ትተው ከቤት ይቀመጣሉ?

መልሱ አንድ እና አንድ ነው፤ ከቫይረሱ ስርጭት አንፃር ምርጫው ህክምና ባልተገኘለት በዚህ ቫይረስ ተይዞ … ተገቢውን የህክምና ክትትል ሳያገኙ መሞት (ከፍተኛ አቅም ያላቸው ሀገራት እንኳን በቫይረሱ ለተያዙት ሰዎች በቂ ህክምና ለመስጠት እየቸገራቸው እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡) ወይም … የለመደብንን የድህነት ኑሮ ፣ ያለችንን እያብቃቃን … የሚመለከታቸው አካላት ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የሚያደርጉት ጥረት እስኪሳካላቸው ድረስ … ራሳችንን ጨቁነን በህይወት ለመትረፍ መፍጨርጨር፡፡

በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን አንድ ከሰው ልጅ ባህሪይ ውስጥ ፣ ብዙ ሰው በቀላሉ እርግፍ አድርጎ ሊተወው የማይችል ነገር እንዳለ ይሰማኛል፡፡ ወሲብ፡፡ አካላዊ (ማህበራዊ) ፈቀቅታን የሚተገብሩም ሆነ ፣ ችላ ብለው አሁንም የተለመደውን የዕለት ተዕለት ኑሮአቸውን የሚመሩ ሰዎች በቀላሉ ለመተው ከሚቸገሩባቸው ባህሪያት አንዱ ነውና፡፡

ወሲብ በተለይም በዚህ በCOVID-19 ወቅት ለጤና እጅግ አሳሳቢ ነገር ነው፡፡ ቢቻል ለቫይረሱ ፈውስ እስኪገኝ ፣ ወይም ስርጭቱ በመጠን እስኪቀንስ ድረስ ሙሉ በሙሉ አካላዊ ንክኪን በማስወገድ  – ወሲብን ጨምሮ – ሌሎች አካላዊ ንክኪን የማይፈልጉ መንገዶችን በመጠቀም የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የራስን አስተዋፅዖ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡

ነገር ግን ፣ የኛ የሰዎች ባህሪይ የታወቀ ነውና ፣ አንዳንዴም ፣ በተለይም ለአንዳንድ የህብረተሰባችን ክፍሎች ወሲብን ለማስወገድ ቀላል ስለማይሆን እና ብዙ ጊዜም መሳሳቶች ሊያጋጥሙ ስለሚችሉ ፣ ሰሞኑን በዚሁ ዙሪያ አንዳንድ ነገሮን ለማግኘት .. የተለያዩ ፅሁፎችን በማነብበት ሰዓት የኒው ዮርክ ከተማ የአካላዊና እና አዕምሮአዊ ጤና ክፍል ያወጣውን ወቅታዊ የሆነ ደህንነቱ የተጠበቀ ወሲባዊ ግንኙነት ማስታወሻ (Memo on Safer sex) አገኘሁና ወደ አማርኛ ገልብጬ ላካፍላችሁ ወደድኩ፡፡

ወሲብ መፈፀም እንችላለን?

ባናደርገው ይመረጣል፡፡ የግድ ማድረግ ካለብን ግን የሚከተሉትን አማራጮች እንከተል፡፡

ሀ. ወሲብ ማድረግ ካለብን ከማን ጋር እናድርግ ?

  • በዚህ ወቅት የመጀመሪያው እና ደህንነቱ የተጠበቀው የወሲብ አጋርዎ … ራስዎ ነዎት፡ ከራስ ጋር የሚደረግ ወሲብ (ወይም ሴጋ (Masturbation)) የኮሮናን ቫይረስ አያስተላልፍም፡፡ በተለይም እጅዎትን (እና ሌሎች የሴክስ መገልገያዎችን) በተገቢው መንገድ ለ20 ደቂቃዎች ያህል ከወሲብ በፊት እና በኋላ በደንብ ከታጠቡ፡፡
  • በሁለተኛ ደረጃ ደህንነቱ የተጠበቀ የወሲብ አጋርዎ ፣ አብሮዎት በፍቅር ፣ በትዳር ፣ በወሲብ ጓደኝነት ከእርስዎ ጋር የሚኖር ሰው ነው፡፡ በጣም የተገደበ የወሲብ ህይወት በዚህ ጊዜ የኮሮና ቫይረስን መዛመት ይቀንሳል፡፡ ቢቻል ከአንድ የወሲብ አጋር ጋር ብቻ ይሁኑ፡፡
  • ከቤትዎት ውጪ ካለ ሰው ጋር የቅርብ የሆነ አካላዊ ንክኪን – ወሲብን ጨምሮ – ያስወግዱ፡፡ ከተለያዩ የወሲብ አጋርዎት ጋር ወሲብ መፈፀምዎን መቀጠል የሚፈልጉ ከሆነ ፣ ቢያንስ ቁጥራቸውን በተቻለ መጠን ይቀንሱ፡፡
  • አብዛኛውን ጊዜ በርከት ካሉ የወሲብ አጋሮች ጋር የመዋሰብ ልምድ ከነበረዎት ፣ አሁን ለጊዜው ረፍት ይውሰዱ፡፡ በቪዲዮ ጥሪ ፣ በፅሁፍ መልዕክት … ወይም በሌሎች አካላዊ ንክኪን በማይጠይቁ የመገናኛ ዘዴዎች የሚደረግ ወሲብን ይምረጡ፡፡

ለ.  በወሲብ ጊዜ ከፍተኛ ጥንቃቄን ያድርጉ

  • መሳሳም COVID-19ንን በቀላሉ ሊያስተላልፍ ይችላል፡፡ መሳሳም ካለብዎት በቤትዎ ከእርስዎ ጋር ካለ የትዳር ፣ የወሲብ ወይም የፍቅር አጋርዎ ውጪ ማንንም አይሳሙ፡፡
  • ሪም ማድረግ ( የአፍ እና የፊንጢጣ ንክኪ) ያስወግዱ፡፡ ሰገራ የ COVID-19 ቫይረስ ተሸካሚ መሆኑ ተረጋግጧልና ፣ በወሲብ ጊዜ ይህን የወሲብ ዓይነት ያስወግዱ፡፡
  • ኮንዶሞች እና ዴንታል ዳም (በአፍ እና በእምስ ወይም ፊንጢጣ መካከል የሚደረግ መከላከያ) የምራቅን እና የሰገራን ንክኪ ፣ በተለይም በአፍ እና በፊንጢጣ በኩል ለሚደረግ ወሲብ በደንብ ይጠቀሟቸው፡፡
  • ከወሲብ በፊት እና በኋላ ሙሉ ሰውነትን በደንብ መታጠብ ከመቼውም ጊዜ በላይ አስፈላጊ ነው፡፡
    • እጆችዎን በሳሙናና በውሃ ቢያንስ ለ20 ሴኮንዶች መታጠብ
    • ሌሎች የወሲብ መገልገያ መሳሪያዎችን በሳሙና እና በሙቅ ውሃ በደንብ ማጠብ
    • ከሌሎች ጋር የሚጋሯቸው እና በቪዲዮ ጥሪ ፣ በፅሁፍ መልዕክት ወይም ሌላ ዘዴ ለሚደረግ ወሲብ የሚጠቀሟቸውን ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች በደንብ ማፅዳት፡፡

ሐ.  አብሮዎት ያለ የትዳር ፣ የፍቅር ፣ የወሲብ ወይም ሌላ አጋርዎ ጤንነት ካልተሰማቸው ፣ ወሲብን አይሞክሩት

  • እርስዎ ወይም አጋርዎ የ COVID-19 ቫይረስ ተጠቂ ሊሆኑ ይችላሉና ፣ ወሲብን ያስወግዱ … በተለይም መሳሳምን፡፡
  • ደህንነት ወይም ጤነኝነት እየተሰማዎ ካልሆነ ፣ የ COVID-19 ምልክቶችን ማለትም፡ ከፍተኛ ትኩሳት ፣ ሳል ፣ ደረቅ ጉሮሮ እና የአተነፋፈስ ችግር ሊያጋጥሙዎት ይችላሉና …. ንክኪን ያስወግዱ
  • እርስዎ ወይም አጋርዎ COVID-19ን ወደ አስጊ ደረጃ የሚያደርሱ ሌሎች የጤና ጉዳዮች ካለብዎት ፣ ወሲብን ለጊዜው እንድታቆሙ ይመከራል፡፡ የጤና ሁኔታዎች ለምሳሌ፡ የሳንባ በሽታ ፣ የልብ ሕመም ፣ የስኳር በሽታ ፣ ካንሰር ወይም የተዳከመ በሽታን የመከላከል አቅም (ለምሳሌ ኤች አይ ቪ ፣ እና ዝቅተኛ የ CD4 ቁጥር ያለው) ያጠቃልላል፡፡

እነዚህን ጠቋሚዎች በመጠቀም ራስዎን ፣ አጋርዎን ፣ ቤተሰብዎን ብሎም አካባቢዎን ከ  COVID-19 በመታደግ ስርጭቱን መግታት ይችላሉ፡፡ እንደ ግራይንደር ፣ ቲንደር  ወይም ሌላ የግንኙነት (ለሴክስም ይሁን ለጓደኝነት) መድረኮች ላይ ያለንን እንቅስቃሴ ፣ ወይም ጅንጀናዎቻችንን ፣ ከጅንጀና ሳይዘል ወደ የአካል ግንኙነት ባናዘልለው መልካም ነው፡፡

መልካም ጊዜ!

ምንጭ፡ https://www1.nyc.gov/assets/doh/downloads/pdf/imm/covid-sex-guidance.pdf

ፎቶ፡ ከ drugtargetreview.com የተገኘ