አንድ አጋጣሚ

በታደሰ ሊበን – 1952

ዜጎችዬ … እንዲሁም ሌሎች አንባቢዎቼ፡ ባለፈው ቃል በገባሁት መሠረት … በ 1952 ከታተመው የታደሰ ሊበን ከ “ሌላው መንገድ” የአጫጭር ልብወለዶች መድብል ውስጥ  “አንድ አጋጣሚ” የሚለውን እና ስለ ተመሳሳይ ጾታ ተማርኮ የሚያወሳውን አጭር ልብወለድ እንደወረደ እነሆ፡፡

ርዕስ፡ አንድ አጋጣሚ (ሌላው መንገድ – ከገፅ 55-74)

በታደሰ ሊበን – 1952

(ፅሁፉን ሙሉ በሙሉ ከመገልበጥ የዘለለ … ባለቤትነቱ የእኔ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ)

———————————————————————————-

I

እኔ በዚያን ጊዜ የምሠራው በኢት/መንግሥት ባንክ ውስጥ ነበር፡፡ ትምህርት ቤት ትቼ ሥራ ከያዝኩም ገና ሁለት ዓመቴ ነበር፡፡ ዕድሜዬም ሃያ አንድ ዓመት ነበር፡፡ ደም ግባቴም በጣም ቆንጆ ነበር፡፡ ይህም ደግሞ የማይካድ የሚያውቁኝ ሁሉ የሚያረጋግጡት እውነት ነበር፡፡ እኔም አሁን ሳላፈገፍግ ስለርሱ ፣ ስለራሴ እንደዚህ ደፍሬ የማወራው እውነት በመሆኑ ነው፡፡ ቀጥ ያለ አፍንጫ ፤ ትክክል የሆኑና ንጣታቸው በረዶ የመሰሉ ጥርሶች ፤ እጅግም ያልወፈሩ እጅግም ደግሞ ያልሳሱ መካከለኛ ከንፈሮች ፤ ቅንድቦቼ ትክክል መሆናቸውና መጥቆራቸው ሰዎችን ተኩሏል ወይም ተከርክሟል አሰኝተው የሚያወራርዱ ፤ ጸጉሬ ፣ ግንባሬ ፣ ጉንጮቼ ፣ ጆሮዎቼ እምንም ዘንድ ያልተዛቡ ፤ በጠቅላላው የሠራኝን እጅ ረቂቅነት አጉልተው የሚያወሱ ነበሩ፡፡ ለሴቶችም የማይችሉት ፈተና ነበርኩኝ፡፡  የትም ይሁን ፣ ማም ይሁኑ ሲያዩኝ መተርከክ ፣ ማተኮር ፣ መገላመጥ ግዴታቸው ነበር፡፡ ብዙ ጊዜ ብዙ ደህና ደህና ሴቶች ራሳቸውን ስተው ሲያተኩሩብኝ ፣ ሲገላመጡብኝ እይዛቸው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ጨርሼ ፍፁ ቆንጆ አልነበርኩም፡፡ በዚያን ጊዜ ከአንድ ሁለት በጣ ቀረብ ብለው ከሚያውቁኝ ልጃገረዶች አፍ እንዳገኘሁት ከውበቴ አንድ የሚጎድለኝ ነገር ነበር፡፡ እሱም እነሱ እንዳሉት የሚጎድለኝ በጣም ትንሽ ነበር፡፡ ጉድለቱም ደግሞ ቁመት ላይ ነበር፡፡ “አህ! ብርሃኑ … ትንሽ ያውም ብዙ አይደለም ፣ ለዓመል ትንሽ ከአሁኑ ዘለግ ብትል ኖሮ ፡ በዚህ ሁሉ ላይ…!”  ይሉኝ ነበር፡፡ ሆኖም በዚህ ጊዜ ዕድሜዬ ገና ሃያ አንድ ዓመት ነበርና በጣም ለመርዘም እንኳን እርግጠኛ ባልሆን ቅሉ ፡ እነዚያ ልጃገረዶች ያሏትን ያህል ትንሽ ለመርዘም ብዙ ተስፋ ነበር፡፡

ይሁንና እኔ ያኔም ሆነ አሁን በዚህ ፈጣሪዬ በሰጠኝ መልክ የምኮራ አልነበርኩም፡፡ እንዲውም ይበልጡን ጊዜ እሱን ለመቀነስና ከሰው መካከል ያልተለየሁ ሆኜ ለማለፍ ስል ጺሜንና ሪዜን ከሚገባው በላይ አሳድግ ፣ ልብስም ስለብስ እያለኝና እያወቅሁበት እንደሌለውና እንደማያውቅበት ሰው ሆኜ እዝረከረክ ነበር፡፡ ይህም ለኔ ለመንፈሴ ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ሆኖም ሰው ተፈጥሮው ሆኖ ቀን ከቀን ወይም ሳምንት ከሳምንት ወይም ወር ከወር በአንድ አሳብ ብቻ አይኖርም፡፡ እንደዚሁም እኔ አንዳንድ ጊዜ አልፎ አልፎ ሲያሰኘኝ ወይም አን ሁኔታ ሲያጋጥመኝ ደህና ሆኜ ፣ጸድቼ ደግሞም ደህና ደህና ልብሴን ለብሼ እወጣ ነበር፡፡ እንደዚሁም ይህ አሁን “አንድ አጋጣሚ” ብዬ ላወራው የተነሣሁት ታሪክ በሆነበት ቀን ጧት ከቤት ደህና ደህና ልብሶቼን ለብሼ ወጥቼ ነበር፡፡

ይኸውም ቀን የ1952 ዓ.ም አንድ ሰኞ ዕለት ነበር፡፡ የዛሬው ሁኔታዬ ከአንድ ከእንግዳ ሰው ጋር ያስተዋውቀኛል ወይም አንዲት ቆንጆ ሴት ልጅ ያስማርከኛል በሚል ወይም እሱን በመሳሰለ መንፈስ ሳይሆን ጧት አልጋዬ ላይ እንዳለሁ ብቻ እንዲሁ ብድግ አድርጌ “ዛሬ ደህና ሆኜ ፣ ደህና ደህናውን ልብሴን ለብሼ እወጣለሁ፡፡” አልኩኝ፡፡ ወሲያውኑም ብድግ ብዬ መጸዳዳትና መለባበስ ጀመርኩኝ፡፡ ጨርሼም ወደ ሥራዬ ለመሄድ ስወጣ በጣም አምሬ በመስከረም ወር ከሌሎቹ ቀደም ብሎ የፈነዳ አደይ አበባ ወይም ፀሐይ በተለይ በሱ ላይ ብቻ ፈንጠቅ ያለበት ጽጌረዳ መስዬ ነበር፡፡ ይህም ደግሞ እውነት ነበር፡፡ ኮቴ አሁን እንኳን ያኔ ለብሼው የተነሳሁት ፎቶግራፉ እቤት አለኝ፡፡ ሽሮማ ፈረንጆች የሰይጣን ቆዳ ከሚሉት ጨርቅ የተሰፋ ሱሪዬ ለኮቱ የሚስማማ ዳለችማ ፣ ገበርዲን ሸሚዜ ነጭ አሚዶ በሚሉት ነጭ ዱቄት የተተኮሰ ፣ ጫማዬ ቡና መልክ ፣ ደግሞም ሾጣጣ ክራቫቴና የእግር ሹራቦቼ ደግሞ በልብሶቼ መልክ ግጥም የሆኑ ነበሩ፡፡ ጸጉሬም ልቆረጠው ስምንት ወይም አሥር ቀን ሲቀር በሚሆነው በሚያምርብኝ ሁኔታው ነበር፡፡

በመንገድም ብዙ ሴቶች ተገላመጡብኝ፡፡ ቢሮም ስገባ አብረውኝ የሚሠሩ ልጃገረዶ መንሾካሾክ ጀመሩ፡፡ ሹክሻኬውም ያው የማውቀው “ እንዴት ቆንጆ ነው ፣ እንዴት ያምርበታል ፣ እንዴት ይቀበለዋል!” የሚል ነበር፡፡ እኔ ግን እንደ ወትሮው ዝም ብዬ ሥራዬን እሠራ ነበር፡፡

እዚህ መሥሪያ ቤት በነዚሁ በአገለገልኩባቸው ሁለት ዓመታት ውስጥ ብዙ ልዩ ልዩ የሥራ መስመር የያዙ ክፍሎች ውስጥ እየተዘዋወርኩ ሠርቼ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ደግሞ የምሠራው የደንበኞች የቼክ ሂሳብ የሚያዝበት ክፍል ውስጥ ነበር፡፡ የተለየ ሥራዬም ደንበኞች ከሂሳባቸው ላይ ገንዘብ ሊያወጡ ሲመጡ ቼኩ ልክ መጻፉን (ይኸውም ማለት ቀኑ ከዚህም በላይ ገንዘቡ በፊደልና በአሐዝ ልክ መጻፉን፣ ፊርማቸው ልክ መሆኑን) መመልከትና ከዚያ በኋላ ደንበኞቹ ወደ ግምጃው ቤት አልፈው ገንዘቡን እንዲወስዱ ተራ ቁጥር ሰጥቼ ቼኩን ደግሞ ሂሳቡን ወደሚይዙት ልጆች ክፍል ከሂሳቡ ላይ ተቀናሽ እንዲያደርጉና ወደ ግምጃው ቤት እንዲያስተላልፉ መላክ ነበር፡፡ በዚሁም ጧት ይህንኑ ሥራ ሰው በዝቶ ያላንዳች ፋታ እሠራ ነበር፡፡ አምስት ሰዓት ሲሆን ሰው መቃለል ጀመረ፡፡ እንዲሁ አንዳንደ ሰው ብቻ አልፎ አልፎ ይመጣ ጀመር፡፡ አምስት ሰዓት ተኩል ላይ ደግሞ ሰው መምጣት ጨርሶ አቁሞ እሩብ ሰዓት የሚያህል ጊዜ ያላንዳች ሥራ አርፌ እንደተቀመጥኩ ፣ አንድ ጠና ያለ የቀይ ዳማ ደግሞም ደህና ደህና ልብስ የለበሰ ሰው መጣ፡፡ እሱም ቀኑን ጠይቆኝ ነግሬው ቼኩን እዚያው ፊቴ ጽፎ ሰጥቶኝ እኔ ደግሞ መርምሬ የመለያ ተራ ቁጥሩን ቀለበት እንደሰጠሁት ቀጠል አድርጎ …

“እባክህ ደግሞ ከሂሳቤ ውስጥ ይህ ቼክ ከወጣ በኋላ ምን ያህል ገንዘብ እንደሚቀረኝ ለማወቅ እፈልግ ነበር?”  ብሎ ጠየቀኝ፡፡

እኔም በዚህ ጊዜ ብድግ ብዬ ይህንኑ ላይለት መጻፊያ ብጫቂ ወረቀት ይዤ ሂሳቡን የሚይዙት ልጆች ወደ አሉበት ክፍል ገባሁኝ፡፡ እዚያም ቼኩ ከተቀነሰለት በኋላ ሂሳቡ ውስጥ የቀረውን ገንዘብ ከመዝገቡ ላይ ተመልክቼ ደግሞም ይህንኑ ለሰውዬው በጽሑፍ ለመስጠት የያዝኳት ወረቀት ላይ አስፍሬ ይዤ ስመለስ ሰውዬው መዝገብ ቤቱንና የኔን ክፍል ከምታገናኘው ትንሽ በረንዳ መሳይ መተላለፊያ ክፍል ውስጥ መጥቶ ብቻውን ቆሞ ሲጠብቀኝ አገኘሁት፡፡ ወዲያውኑ የሂሳቡን ልክ በቃሌ ነግሬው ደግሞም የጻፍኩባትን ወረቀት ሰጠሁት፡፡ እሱም ወረቀቷን”እግዚአብሔር ይስጥልኝ” ብሎ ተቀብሎኝ አየት አድርጎ ኪሱ ከከተታት በኋላ ቀጠል አድርጎ፣ አሁን ደግሞ …

“እባክህ አንተ ዘንድ ደግሞ ጉዳይ ነበረኝ፡፡” አለኝ፡፡ እኔም ሰውዬውን ከዚያ በፊት አይቼው ባለማወቄ ደንግጬ..

“ምን ..ጌታዬ ?” ብዬ ጠየቅሁት፡፡

“እዚህ መቼም የሥራ ቦታ ነው፡፡ እንደልብ ለመነጋገር አይቻልም፡፡ ደግሞም ማስቸገር አይገባም፡፡ ከሥራ ውጭ ላገኝህ የምችልበት ቦታ ድረስ ቀጠሮ ብትሰጠኝ እመጣ ነበር፡፡”  አለኝ፡፡

እኔም በዚህ ጊዜ ይህን የሚያህል ትልቅ ሰው የት ብዬ እቀጥራለሁ በማለት ደነገጥሁኝ፡፡ ስለዚህ ወዲያው ቀጠል አድርጌ እየተርበተበትኩ ደግሞም በአንድ ወገን በሚቻለኝ ፈገግ እንደማለት ሞክሬ …

“እኔ የት ቦታ እቀጥርዎታለሁ፡፡ እርስዎ ያሉ ቦታ ይንገሩኝና እኔ እመጣለሁ፡፡” አልኩኝ፡፡

እሱም በዚህ ጊዜ…

“እኔ ቤት ለመምጣት ትችላለህ?” ብሎ ጠየቀኝ፡፡

እኔም መልሼ፡

“ስፍራውን ከአወቅሁ ምን ቸገረኝ፡፡” አልኩኝ፡፡

ወዲያውኑም ሰውዬው ሠፈሩንና የቤቱን ምልክት ምልክቱን በፍጥነት ነግሮኝ እዚያም ከምሽቱ አንድ ሰዓት ላይ እንድገኝ ቀጥሮኝ ሄደ፡፡

II

እኔም ከዚያች ሰዓት አንስቶ ቀኑን ሙሉ ዝም ብዬ ስለዚሁ ቀጠሮና ስለሰውዬው ሳስብ ዋልኩኝ፡፡ “ይህ ሰው እንደዚህ ያለኝ እኔ የማደርግለት ከቶ ምን ነገር አለና ነው?” ብዬ አሰብኩኝ፡፡ አቅሜንና ልኬን ደጋግሜ በማሰብና በመገመት ደግሞ .. “እኔ ለእንደሱ ያለ ትልቅ ሰው ደግሞም ትልቅ ደንበኛ ምን ጠቃሚ የሆነ ነገር የማደርገው ከቶ አለ?” አልኩኝ፡፡ ሆኖም ይህንኑ አሳቤንና ደግሞም ቀጠሮዬን ለማንም ሰው ሳላካፍል ሰዓቱ እስኪደርስ ብቻ ዝም ብዬእንደዚሁ ነገሩን ብቻዬን በሆዴ ሳፍተለትል ውዬ አሥራ ሁለት ሰዓት እንደሆነ ደግሞ ወደ ቤቱ ሄጄ ከትልቅ ሰው ፊት እንደምቀርብ አኳኋን ፊቴን አወዛዝቼ ልብሴም በደንብ መሆኑን በመስተዋት ውስጥ አይቼ ጸጉሬን ቀና ቀና አድርጌ ሳበቃ ወደ ቀጠሮዬ ቦታ ጉዞ ቀጠልኩኝ፡፡ መንገዱንም ቆጥቤ ሄጄ ልክ አንድ ሰዓት ከአምስት ደቂቃ ሲሆን ምንም ሳላሳስት ምልክቱን ልብ እያደረግሁ ተራምጄ እዚያ ደረስኩኝ፡፡ ምልክቱ በውል የተነገረኝን አጥር ግቢ እንዳየሁ ወደ አጥሩ በር ጠጋ ብዬ በረኛውን፡…

“ወንድሜ ይህ የአቶ ፐ … ቤት አይደለም ወይ?”  ብዬ ጠየቅሁ

እሱም አንድ ጊዜ ከላይ እስከታች ተመልክቶኝ ..

“አዎን፡፡” ብሎ መለሰልኝ፡፡

ቀጥዬም … “ እቤት አሉ ወይ?” ብዬ ጠየቅሁት፡፡

እሱም… “አዎን አሉ፡፡” አለኝ፡፡

እኔም ቀጥዬ… “ቀጠሮ ነበረኝ ብትነግርልኝ?” አልኩት፡፡

እሱም መልሶ… “ማን ልበል?” አለኝ፡፡

“ያውቃሉ፤ አንድ እባንክ የሚሠራ ልጅ ነው በላቸው፡፡” አልኩት፡፡

እሱም ወዲያው ፈጥኖ ሄዶ ከዚያም ወዲያው ተመልሶ መጥቶ ሰንሰለቱን ከበሩ ላይ ፈትቶ …

“ይግቡ!” አለኝ፡፡

III

ቤቱ ውስጡ በጣም የሚያምር ነበር፡፡ ገና ዋናውን በር ሲገባ የሚገኘውም የእንግዳ ቤቱ ነበር፡፡ የግድግዳ ወረቀቱም በጣም የሚያምር ነበር፡፡ ክፍሉም አሁን ዓይነቱ መልህቅ በሚመስል ብዙ አምፑሎች በተሸከመ መቅረዝ በርቶ ነበር፡፡ ሲገባ በስተግራ በኩል ወደ ምዕራባዊው ግድግዳ ሲል ትልቅ በጣም የሚያምር ሥጋጃ ወለሉ ላይ ተነጥፎ በላዩም ላይ ዓይነታቸው ከፍ ያለና የሚያማምሩ ሙሉ ሶፋዎች ተደርገውበት ነበር፡፡ ከዚያም ትንሽ እልፍ ብሎ ግድግዳው ጥግ አንደኛው ማዕዘን ዘንድ አንድ ትልቅ ሬዲዮ ግራማፎን ነበር፡፡ ከክፍሉ በስተቀኝ በኩል ደግሞ እንደዚሁ ወደ ግድግዳው ሲል አንድ ድንክ አልጋ ፍራሹ ሽንሽን አበባማ ጨርቅ የለበሰ ይታይበት ነበር፡፡ እወለሉም ላይ በዓይነቱ ልክ ያንኑ በስተግራ በኩል ሶፋዎቹ ስር የተነጠፈውን የሚመስል ስጋጃ ተነጥፎ ነበር፡፡ ግድግዳው ላይ ከዚሁ አልጋ በላይ ወደራስጌው በኩል ሲል ደግሞ አንድ ትልቅ የሚወዛወዝ ረጅም የሰዓት መቁጠሪያ ያለው የግድግዳ ሰዓት ነበር፡፡ ይህም ሰዓት በየሩብ ሰዓቱ ላይ አንድ ዓይነት ጣፋጭ የሆነ ዜማ ያሰማ ነበር፡፡ ይህንንም ያወቅሁት እኔ ስገባ አንድ ሰዓት ተሩብ ሆኖ ነበርና የደቂቃው መቁጠሪያ ተሩብ ላይ እንዳረፈ በዜማ ደወለ፡፡ ግድግዳው ላይ እንደዚሁ ብዙ ልዩ ልዩ ፎቶግራፎች ደግሞም የሚያማምሩ የእጅ ስዕሎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን ከነዚህ ሁሉ በላይ እዚያ ቤት ገና ሲገባ የሰውን ዓይን የሚስበው እመሀል ከሚገኘው ወደ ሌላው ክፍል ውስጥ ከሚያስገባው በር በላይ ግድግዳው ላይ የተሰቀለ የአንድ የትልቅ ነብር ጭንቅላት ነበር፡፡ የሱም የአፉ አከፋፈትና የዓይኖቹ መፍጠጥ ትኩር ብለው ሲመለከቱት ተፍስ ያለው መስሎ በጣም ያስፈራ ነበር፡፡

እኔንም በረኛው አጥር ግቢውን እንዳስገባኝ ከቤቱ በር ላይ የተቀበለኝ ሰውዬው ራሱ ነበር፡፡ አቀባበለም እንዲህ አልነበረም፡፡ በጣም ከፍ ያለና ትሕትና የሞላው ነበር፡፡ እጁን ዘርግቶ ጨብጦኝ እንደምን አመሸህ ካለኝ በኋላ እጄን ሳይለቀኝ ግራ እጁን ትከሻዬ ላይ ጭኖ ወስዶኝ ፣ ከዚህ በላይ የገለጽኳቸው ሶፋዎች አንዱ ምቹው ላይ አስቀመጠኝ፡፡ ወዲያውም እስካሁን ወደስፍራው ሳይመለስ በረንዳው ላይ ቆሞ ለቀረው ዘበኛ ሄዶ ዝቅ ባለ ድምጽ አንድ ነገር ነግሮ ካሰናበተና በሩን ከዘጋ በኋላ በፈገግታ እኔ ዘንድ ተመልሶ መጥቶ –

“ታዲያ ምን ትጋበዛለህ? ሁሉ ነገር አለ፡፡ ድንገት አንተ የምትፈልገው ነገር እቤት ባይኖም ሱቁ ቅርባችን ነው ልጅ ሄዶ ይገዛል፡፡” አለኝ፡፡

እኔም ወዲያውኑ በትሕትና መልሼ… “ኧረ ግድ የለም! እቤት ያለውን ማንኛውንም ነገር እጋበዛለሁ፡፡” አልኩኝ፡፡

እሱም በዚህ ጊዜ..

“መልካም እንግዲያውስ እቤት ያለውን ማንኛውንም ከተጋበዝክ ውስኪ ብትጋበዝ ደስ ይለኛል፡፡ ምክንያቱም እኔም እሱን ነው የምጠጣው፡፡” አለኝ፡፡

እኔም በትሕትና መልሼ… “እሺ፡፡” አልኩኝ፡፡

እሱም ወዲያውኑ ክፍሉ መሀል ከነብሩ ጭንቅላት ሥር የሚገኘውን በር ከፍቶ ወደሚቀጥለው ክፍል ገባ፡፡ ከዚያም በአንድ ወንድ አሽከር ውስኪውንና ብርጭቆዎቹን ደግሞም የሶዳውን ጠርሙሶች አስይዞ መጣ፡፡ አሽከርዬውም የሶዳውን መክፈቻ ረስቶት ኖሮ አንዲት መልከ ቀና ሴት ልጅ ተከትላ መጥታ በበሩ ብቅ ብላ አሽከርየውን በስሙ ጠርታ መክፈቻውን ሰጠችው፡፡ እሷም ይህንን ስታደርግ ባገኘችው ትንሽ ጊዜ እኔን ከእግር እስከራሴ ተመለከተችኝ፡፡ ሰውዬውም የእሷ መምጣት ደስ እንዳላለው ሁኔታው ገልጾት ነበር፡፡ አሽከርዬው መጠጦቹንና ብርጭቆዎቹን ከኔ ፊት ከሶፋዎቹ መሀል ከአለው እንቁላልማ ጠረጴዛ ላይ ገና እንዳስቀመጠ … ሰውዬው በሩን ዘግቶ እንዲሄድና ደግሞም ማንም ሰው ወደዚህ እኛ ወዳለንበት ክፍል ዝር እንዳይል እንዲነግር አዘዘው፡፡ እሱም የተባለውን ሊፈጽም እጅ ነስቶ “እሺ፡፡” አለ፡፡  ሆኖም በሩን ዘግቶ እስኪወጣ ድረስ እሱም እኔን በተቻለው ከሰውዬው እየተሰረቀ ይመለከተኝ ነበር፡፡ በኋላም ከሰዓቱ ትክ ትክ በስተቀር ሁለታችን ብቻ በክፍሉ ውስጥ እንደቀረን ሰውዬው አጠገቤ ከፊት ለፊቴ ቁጭ ብሎ ውስኪውን መቅዳት ጀመረ፡፡ ወዲያውም የሶዳውን ውሃ ከልሶ ሁለታችንም ብርጭቆ ብርጭቋችንን አንስተን .. “ለጤናችን” በሚል መንፈስ እሱ ብርጭቆውን ዓይን ዓይኔን እየተመለከተኝ ወደፊቱ ካነሳው በኋላ እኔም እንደዚሁ አንስቼ አንድ አንድ ተጎነጨን፡፡ መልሰንም ቁጭ ስናደርግ እሱ ንግግር ጀመረ፡፡

“ብዙ ጊዜ ነው ላነጋግርህ ስመኝ፡”   አለኝ፡፡

እኔም ምንም ሳልመልስ ብቻ በዚሁ የቱን ያህል ክብር እንደሚሰማኝ ለመግለጽ ፈገግ ብዬ ዝም አልኩኝ፡፡

ቀጥሎም … “ስንት ጊዜህ ነው ባንክ ስትሠራ?” ብሎ ጠየቀኝ፡፡

እኔም … “ሁለት ዓመቴ ነው፡፡” ብዬ መለስኩኝ፡፡

“ብዙ ጊዜ አይደለማ፡፡” አለኝ፡፡

“አዎን ጥቂት ጊዜ ነው፡፡” አልኩኝ፡፡

ለጥቂት ጊዜም ምንም ሳንነጋገር ዝም አልን፡፡ በኋላም እሱ…

“ጠጣ እንጂ” ብሎ ብርጭቆዬን አንስቶ ሰጠኝ፡፡ እኔም ብርጭቆውን እጅ ነስቼ ተቀብዬ ወደ አፌ ወስጄ ተጎንጭቼ ቁጭ አደረግሁኝ፡፡ ከዚህም በኋላ ደግሞ ምንም ሳንነጋገር ዝም ብለን ጥቂት ጊዜ አለፈ፡፡ በኋላም ሰውዬው ድንገት ሳላስበው ግራ እጄን በቀኝ እጁ ነካኝ፡፡ እኔም ደነገጥኩኝ፡፡ ሆኖም ሳያውቅ ይሆናል እንደተገነዘበ ይቅርታ ጠይቆኝ ያነሳዋል ብዬ ድንጋጤን ውጬ ተጠባበቅሁኝ፡፡ ነገር ግን ሰውዬው የተጠባበቅሁትን አንዱንም ሳያደርግ እንዲያውም ይህንኑ እጄን ጎትቶ ወስዶ ሰዓቴን ሲመለከት ከቆየ በኋላ ወደ እኔ ቀና ብሎ…

“ይህ ምን የሚሉት ሰዓት ነው? ጥሩ አይደለም፡፡ እኔ ጥሩ ሰዓት በቅርብ ጊዜ ውስጥ ከኤደን አስመጣልሃለሁ፡፡” አለኝ፡፡

እኔም ምንም ልል አልቻልኩም፡፡ እጄን በተቻለኝ በጨዋ ደንብ ከሱ ዘንድ ጎትቼ ወስጄ ለችሮታው ደግሞ እግዚአብሔር ይስጥልኝ በሚል መልክ ፈገግ ብዬ እጅ ነሣሁኝ፡፡

ቀጥሎም…. “ይህ እዚህ ታች ብትን ሱፍ ጨርቅ የሚሸጠውን ሰውዬ አይተኸው የለም?” ብሎ ጠየቀኝ፡፡

እኔም ቦታውን አውቀው ደግሞም አሁን ስመጣ ሰውዬውን አይቼው ነበርና ደግሞ ምን ሊል ነው በማለት ግራ ገብቶኝ…. “አዎን” አልኩኝ፡፡

“ነገ መጥተህ የሁለት ሙሉ ልብስ ጨርቅ መርጠህ ለሰውዬው እሱ ነው የላከኝ ብለህ ነግረህ እንድትወስድ፡፡ እኔ ጧት ሳልፍ እነግረዋለሁ፡፡” አለኝ፡፡

እኔም በዚህ ጊዜ ይበልጥ ግራ ገብቶኝ… “ኧረ ግድ የለም!” አልኩኝ፡፡

ሰውዬውም አጠንክሮ … “ለምን? … እንድትወስድ!” አለኝ፡፡

እኔም መልሼ… “እሺ” አልኩኝ፡፡

ይህንንም ብለን ትንሽ ጊዜ ደግሞ ሳንነጋገር ቆየን፡፡ በዚህ ጊዜም ለእኔ ሶስተኛ ብርጭቆ ውስኪ ተቀድቶልኝ ነበር፡፡ ቀጥሎም ሰውዬው ብድግ አድርጎ …

“ለእኔ ደግሞ አንተ የምታደርግልኝ ነገር አለ፡፡” አለኝ፡፡

እኔም በዚህ ጊዜ በሚቻለኝ ፈገግ ብዬ በልዘብታ … “እኔ ላደርግ የምችለው ነገር ከሆነ በደስታ አደርጋለሁ፡፡” አልኩኝ፡፡

ሰውዬውም በዚህ ጊዜ መልሴን በመጠራጠር ይሁን ወይም በሌላ እንጃ ትኩር ብሎ አየኝ፡፡

ከዚህም በኋላ ለጥቂት ጊዜያት አሁንም ሳንነጋገር ዝም ብለን ውስኪ ብቻ እየጠጣን ቁጭ አልን፡፡ እኔም በዚህ ጊዜ የያዝኩት አራተኛ ብርጭቆ ውስኪ ነበር፡፡ በኋላም ሰውዬው አሁንም ብድግ አድርጎ…

“ሁሉ ሰው መቼም ተፈጥሮ ሆኖ አንዳንድ አመል አለው፡፡” አለኝ

በዚህ ጊዜ እኔ ምንም መልስ ሳልሰጥ ዝም አልኩኝ፡፡ ከተል አድርጎ ደግሞ…

“ለምሳሌ አንድ ምሽት ከአንተ ጋር አንድ ጨዋታ ቤት አብረን ሄደን … አንተ ወደ ጓዳ ውስጥ አልፌ መጣሁ ጠብቀኝ ብትኝ ፣ እጠብቅሃለሁ፡፡ ወይም ከዚያ ወደ አንድ ሌላ ሥፍራ ከሴትዮይቷ ጋር በመኪና ውሰደኝ ብትለኝ እወስድሃለሁ፡፡ “ አለኝ፡፡

እኔም በዚህ ጊዜ ደነገጥኩኝ፡፡ በልቤም “ይህ ሰውዬ ዛሬ ምንድነው የሚለው!” አልኩኝ፡፡ ነገር ግን በኋላ መልሼ…

“ኧረ የለም! እኔ እንደዚህ ያለ ቦታ ሄጄም አላውቅ፡፡ ደግሞም ለወደፊት ብሄድም እርስዎን አላለፋም፡፡” አልኩኝ፡፡

“ምን አለበት! እኔና አንተ ከአሁን ወዲያ ሚስጥራችንን የምንካፈል ወንድማማቾች ነን፡፡” አለኝ፡፡

እኔም ለዚህ ምንም ሳልመልስ ዝም አልኩኝ፡፡ በዚህ ጊዜ አምስተኛ ብርጭቆ ውስኪ ተቀድቶልኝ ነበር፡፡ ሞቅታም አንደበቴን ያዝ፣ ምላሴንና ከንፈሮቼን ደንደን ፣ ሰውነቴን ጋል ጋል ማድረግ ይዞ ነበር፡፡ በመጨረሻ ሰውዬው ግራ እጁን እጉልበቴ ላይ አምጥቶ .. አድርጎ…

“አሁን እኔ ቢሮ በመኪና ሄደን እንምጣ፡፡” አለኝ፡፡

እኔም በዚህ ጊዜ ደግሞ ይበልጥ ደነገጥኩኝ፡፡ ምንየቱም የሰውዬው ሁኔታ በዚህ ጊዜ ተለዋውጦ ነበር፡፡ ፍዝዝ ብሎ ትክ አድርጎ ይመለከተኝ ነበር፡፡ እኔም ቶሎ ሰዓቴን ተመልክቼ እፊቴም ላይ በተቻለኝ ፈገግታ ጨምሬ…

“የለም፡ መሽቷል ሶስት ሰዓት ነው፡፡ ቤቶቼ ይሰጋሉ፡፡ ከዚህ በፊት እስከዚህ አምሽቼ አላውቅም፡፡” አልኩኝ፡፡ ውሸቴን ደግሞ ቀጠል አድርጌ ለስለስ ባለ ቃል .. .”ባይሆን እንኳን ነገ አመሻለሁ ብዬ ነግሬ መጥቼ እዚያም ቢሆን በጊዜ ሄደን የሚሠራውን ወይም የሚጻፈውን ነገር እንጽፋለን፡፡” አልኩኝ፡፡

እሱ ግን አሁንም እጁን ከጉልበቴ ላይ ሳያነሳ በልመና ቃል ቀጠል አድርጎ ፡ –

“እኩል ሰዓት እንኳን አይወስድብንም፡፡ አሁኑኑ ደርሰን እንመጣለን፡፡” አለኝ፡፡

እኔ ግን አሁንም ድርቅ ብዬ ፤ “የለም ዛሬ ልሄድ አልችልም፡፡” አልኩኝ፡፡ ቀጥዬም ሰዓቴን ዳግመኛ ተመልክቼ .. “እንግዲህ እቤቴ ልሂድ፡፡” ብዬ ብድግ አልኩኝ፡፡ እሱም “እሺ፡ እንግዲያውስ በመኪና ልሸኝህ፡፡ “ አለኝ፡፡ እኔ ግን አሁንም ውሸቴን … “የለም፣ ግድ የለም መንገዱ ጉራንጉር ውስጥ ነው፡፡ መኪና አያስገባም፡፡” ብዬ እምቢ አልኩኝ፡፡ እሱም ምንም እንዳልሆነለት እንዳወቀ በዚያው ዛሬ እቤቱ በመጣሁበት ሰዓት በማግሥቱ ማታ እዚሁ ቤቱ እንድመጣና ከዚያም ቢሮው እንድንሄድ ቀጠሮ ሰጥቶኝ እኔም “እሺ” ብዬው በር ድረስ ሸኝቶኝ ተጨባብጠን ተለያየን፡፡

IV

የዚያን ዕለት ማታ ለሊቱን በሞላ እንቅልፍ እስኪያሸንፈኝና እስኪወስደኝ ድረስ ደግሞም በማግስቱ ጠዋት ሥራዬ ቦታ ሁሉ ነገሩ ሆዴን ሲበላኝ ዋለ፡፡ በልቤም “ምን ማለቱ ነው ሰውዬው? ምን ማድረጉ ነው ሰውዬው?” አልኩኝ፡፡ ማታም በቀጠሮዬ ሰዓት ዝም ብዬ ሳልሄድ ቀረሁኝ፡፡ መሰንበቻውንም በነገሩ ተክዤ ከረምኩኝ፡፡ በዚያች ማታ ሰውዬው የነበረበትን ሁኔታ ሳስብና ንግግሩን ሁሉ ሳስታውስ መንፈሴ ይታወክና ምን ነገር እንዳምን ደግሞም ምን እንድክድ ይቸግረኝ ነበር፡፡ በአንድ ወገን ደግሞ ቀጠሮውን በማፍረሴና ሰውዬውን ባለማስጨረሴ ፤ ደግሞም እንዲሁ ደርሼ አዕምሮዬን በእንደዚህ ያለ በማይገባ አሳብ በማናወጼ እራሴን መልሼ እሰድብ ነበር፡፡ አንዳንድ ጊዜም እራሴው ለእራሴው ብድግ አድርጌ “ማን ያውቃል! ሰውዬው አንድ ብርቱ ጉዳይ ገጥሞት ፈልጎኝ እንደሆን? ማን ያውቃል … የዳሰሰኝ ደግሞም ላስጊጥህ ያለኝ የተፈጥሮ የገርነት ሁኔታው እንደሆን?” እል በር፡፡ ሆኖም እኔ ይህንኑ ነገር ለማንም ሰው አልተነፈስኩም ነበር፡፡ በሕይወቴ የገጠመኝን ነገር ለማልደብቀው ሁሉንም ለምነግረው ጓደኛዬ እንኳን አልነገርኩትም ነበር፡፡ ምክንያቱም ታሪኩ በዚህ ሁኔታው ገና የተጀመረ እንጂ ያለቀ ወይም ለሰው የሚወራ ነገር አልነበረም፡፡ የሚያልቀውና የሚወራው የዚያን ዕለቱን ማታ ወይም በማግስቱ በቀጠሮዬ ሰዓት ሰውዬው ቤት ሄጄ ከዚያም አብረን ከተባለው ቢሮው ሄደን ቢሆን ነበር፡፡

እኔም እያደር ነገሩን እረሳሁት፡፡ ይህ በሆነም በስምንት ቀኑ ከመሥሪያ ቤቴ የነበረኝን የሁለት ዓመት የሁለት ወር ስንብት ተቀብዬ ለዕረፍት ወደ ውጭ ሄድኩኝ፡፡ ከዚያም በኋላ ሰውዬው በቀጠሯችን ቀን ሳልሄድ በመቅረቴ መሥሪያ ቤት ድረስ ዳግመኛ መጥቶ ይፈልገኝ ወይም አይፈልገኝ አላወቅሁኝም ነበር፡፡ ሆኖም ከጥቂት ወራት በኋላ እኔም ይህንኑ ነገር ለብዙ ጊዜያት ፈፅሞ ረስቼው ጊዜም እንደዚያው እንደማያርመው ልማዱ እየሮጠ ሄዶ ስድስት ወር አልፎ ሳለ ድንገት አንድ ቀን አንድ ነገር ሆነ፡፡ እሱም ደግሞ ይህ የሚከተለው ነበር፡፡

V

ከዕለታት አንድ ቀን ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ በአሥር ሰዓት ተሩብ ላይ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ኮከብ አደባባይ፣ አዲሱ የሸዋ መብራት ኃይል መሥሪያ ቤት ፎቅ ስር ከአንድ ልጅ ጋር ቆመን እናወራ ደግሞም አላፊ አግዳሚውን እንመለከት ነበር፡፡ ልጁም በቁመት ከኔ ዘለግ ያለ በማማርም ከኔ አስር እጅ የሚያመጣ ፣ በጣም ቆንጆ ፣ ደግሞም ደማም ነበር፡ የጥርሶቹም ንጣትና ማማር ምነው አስሬ ፈገግ ባለ የሚያሰኝ ነበር፡፡ ልብሱም ሁልጊዜ ጽዱና ዓይነቱም በጣም ከፍ ያለ ነበር፡፡ እኔም ልጁን ካወቅሁት ገና ጥቂት ጊዜ ነበር፡፡ የተዋወቅነውም አንድ የጠረጴዛ ቴኒስ ውድድር በሚደረግበት ክበብ ሁለታችንም ለግጥሚያ ሄደን ተገናኝተን ነበር፡፡

undefined

ሆኖም በዚሁ ጥቂት ጊዜ ውስጥ ከልጁ ጋር በጣም ተፋቅረን ጓደኛሞችም ሆነን ነበር፡፡ ሲኒማ ቤት ደግሞም ሌላ ልዩ ልዩ የጨዋታ ስፍራም ጨዋታ ለመመልከት አብረን እንሄድ ነበር፡፡ በዚህም ቀን እዚህ ሥፍራ ወደ አንድ ክበብ ሄደን ጨዋታ ለመመልከት ተቃጥረን ፣ በቀጠሮአችንም ሰዓት ተገናኝተን የምንሄድበት ስፍራ ጨዋታው የሚጀምረው አስራ አንድ ሰዓት ላይ ነበርና ፣ ሰዓቱ እስኪደርስ ድረስ እዚሁ ቦታ ቆመን እናወራ ነበር፡፡ በአጠገባችን ስላለፈች ስለ አንዲት ልጃገረድ ሁኔታ ስናወራ ቆይተን ሌላ ደግሞ እንደዚሁ የሚያስወራ ትርኢት ወይም አድራጎት ስንፈልግ ልጁ በድንገት ወደኔ ዘወር ብሎ ንግግር ለወጥ አድርጎ …

“ተመልከት ከኋላህ በኩል በዳለችማ መኪና ከጊዮርጊስ በኩል መጥቶ ወደዚህ የሚጠመዘዘውን ሰውዬ፡፡” አለኝ፡፡

እኔም እንደተባልኩት ወዲያው ዘወር ብዬ ልመለከት ስል ቀጠል አድርጎ ደግሞ…

“የምንነጋገረው ስለርሱ መሆኑን እንዳያውቅብን ዝም ብለህ ተመልከተው እንጂ ወደኔ አትገላመጥ፡፡ ካለፈ በኋላ ነገሩን እነግርሃለሁ፡፡” አለኝ፡፡

እኔም በዚህ ጊዜ ቀስ ብዬ ወደተነገረኝ አቅጣጫ ዘወር አልኩኝ፡፡

እዚያም ዓይነቱ በተነገረኝ መኪና ውስጥ በአየሁት ሰውዬ ደነገጥኩኝ፡፡ ምክንያቱም ሰውዬው ያ እኔ የማውቀው ፣ የዚያን ዕለት ማታ እቤቱ የጋበዘኝና ቢሮውም አብሬው እንድሄድ የጠየኝ ፣ እምቢ ብለውም በማግሥቱ ማታ እንድመጣና እንድንሄድ የቀጠረኝ ነበር፡፡ እሱም እኛን ሳያየን በመኪናው እንዳለፈ እኔ በጥያቄ መልክ ሆኜ ወደ ልጁ ዘወር አልኩኝ፡፡

እሱም በዚህ ጊዜ ወደኔ ተመልክቶ …. “ ሰውዬውን አየኸው አይደለም?” ብሎ ጠየቀኝ፡፡

እኔም በአፌ ምንም ሳልመልስ ነገር ግን አዎን ስል ራሴን ብቻ ወደላይና ወደታች ነቀነቅሁለት፡፡

እሱም በዚህ ጊዜ ቀጠል አድርጎ … “ታውቃለህ.. እሱ ሰውዬ አንድ ቀን ማታ እቤቱ ጠርቶ ወስዶኝ ውሲኪ ሲያጠጣኝ አምሽቶ ያለኝን?” .. አለኝ፡

እኔም.. እንጃ አላውቅም ፣ በአንድ ጊዜ እዚያ ነደደኝ፡፡ ብውም አልኩኝ፡፡ ራሴንም ለመቆጣጠር የቱንም ያህል ብሞክር አቃተኝ፡፡ ብድግ አድርጌም ልጁን እዚያ…

“ውሸታም፡፡ እንዲያው ደርሰህ የሰው ስም አታጥፋ፡፡ ቤቱ ቀድሞ የት እንደሆነ አታውቅም፡፡ እሺ ቤቱ የት ነው? ደግሞስ እንዴት ያለ ነው? እውስጡስ ደግሞ ምን ምን ነገር አለ?” … ብዬ ጠየቅሁት፡፡

እሱም እኔን እንደዚህ በአንድ ጊዜ ለዋውጦ እዚህ ባደረሰኝ ነገር ተገርሞ አተኩሮ እያየኝ በለዘብታ…

“ቤቱ በጣም የሚያምር ነው፡፡ ደግሞም እዚያ ወዲያ ካለው እንጨት ተራ አጠገብ ነው፡፡ እውስጡም…” አለ፡፡ ደግሞም ትንሽ አስቦ “… እውስጡም አንድ ትልቅ የሚወዛወዝ የሰዓት መቁጠሪያ ያለው ፣ በየሩብ ሰዓቱም እየደወለ ዜማ የሚያሰማ ሰዓት ፣ ደግሞም” አለ፡፡ .. አሁንም አስቦ .. “… ደግሞም በአንድ በኩል ግድግዳው ላይ ከአንድ ወደ ሌላ ክፍል ከሚያስገባ በር በላይ የአንድ የትልቅ ነብር ጭንቅላት የተሰቀለ አለ፡፡” አለኝ፡፡

እም በዚህ ጊዜ ምንም አልመለስኩም፡፡ ብቻ አመዴ ቡን ብሎ ኩምሽሽ አልኩኝ፡፡