ኮቪድ-19 እና አዕምሮአዊ ጤና

ኮቪድ-19 እና አዕምሮአዊ ጤና

የኮቪድ-19 (ኮሮና) ቫይረስ ወረርሽኝ በዓለም ላይ በፍጥነት እየተዛመተ እየመጣ ባለበት በዚህ ወቅት ፣ በሕዝቡ ውስጥ በተለይም አዛውንት ፣ አዋቂዎች ፣ የጤና እንክብካቤ አቅራቢዎች ፣ በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ የሚገኙ ሰዎች ፣ ሌላ የጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች እና ከመደበኛው የህብረተሰብ ክፍል ቀድሞውኑም መገለል የሚደርስባቸው የተገፉ የህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ከፍተኛ የሆነ ፍርሃትን ፣ አዕምሮአዊ ጭንቀትን እና ድብርትን እያመጣ ነው።

በሕብረተሰባዊ አዕምሮአዊ ጤና አባባል ፣ እስከአሁን ድረስ የተመዘገበው እያሻቀበ የመጣ ጭንቀት  ወይም ድብርት ቢሆንም ፣ ከዚህ በኋላ የሚተገበሩ አዳዲስ መመሪያዎች ፣ በተለይም ማህበራዊ ፈቀቅታ እና ራስን ለይቶ ማቆየት በብዙ ሰዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች እና ኑሮ ላይ የራሱን የሆነ ከፍተኛ ጫና ስለሚያሳድር … የብቸኝነት ስሜት ፣ ከፍተኛ የሆነ ድብርት (depression)፣ ከልክ ያለፈ የአልኮል እና የመድኃኒት ወይም ዕፅ (drug) ሱስ ፣ አልፎም ራስን የሙጉዳት እና የማጥፋት ስሜት አብረው ያሻቅባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

እንደ ጣልያን ባሉ በከፍተኛ ሁኔታ በኮቪድ-19 የተጠቁ አካባቢዎች ቀድሞውኑ የአዕምሮአዊ ጤና እክል ላለባቸው እንዲሁም በዚህ ወረርሽኝ ምክንያት አዲስ አዕምሮአዊ ጤና እክል ለሚያጋጥማቸው ሰዎች ፣ ወረርሽኙን ለመከላከል ፊት ለፊት ከተጋፈጡት የጤና ክብካቤ አገልግሎት ሰጪዎችን ጨምሮ…. ተገቢውን የአዕምሮአዊ ጤና አገልግሎት መስጠት አሳሳቢ የሆነ ደረጃ ላይ እየመጣ ይገኛል፡፡

እና በዚህ አካላዊ ፈቀቅታ እና ራስን ለይቶ ማቆየት መፍትሔው በሆኑበት የወረርሽኝ ወቅት ካለንበት ሆነን አዕምሮአዊ ጤናችንን እንዴት መጠበቅ እንችላለን? አንዳንድ ነጥቦችን እነሆ፡

  • አካላዊ መራራቅ፡   አካላዊ መራራቅ ከለመድነው ኑሮአችን የሚያስተጓጉለን ፣ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴአችን ዕክል ቢሆንም ዋነኛው ወረርሽኙ የማይተላለፍበት መንገድ መሆኑን ማመን አለብን፡፡ አካላዊ መራራቅ ከእኛ አልፎ የምንወዳቸውን ቤተሰቦቻችንን ፣ ጓደኞቻችንን ፣ የሥራ ባልደረቦቻችንን ፣ ህፃናትን ፣ በዕድሜ የገፉ ሰዎችን… እንዲሁም ሌሎችን ከወረርሽኙ የምንጠብቅበት መንገድ መሆኑን በማወቅ ፣ ወረርሽኙን በመከላከል ሂደት ውስጥ እየተሳተፍን ፣ መልካም ነገር እየሰራን መሆኑን ልንረዳ ይገባል፡፡ ያለንበት ተወስነን በመቀመጣችን ሌሎችን እያዳንን ነውና፡፡
  • መረጋጋት፡   ከምንጊዜውም በበለጠ አሁን ላይ መረጋጋት ያስፈልጋል፡፡ በዙሪያችን ምን እየተካሄደ እንደሆነ ቆም ብሎ ማስተዋል ቀጥሎ ምን ርምጃ መውሰድ እንዳለብን ለመወሰን ይረዳናል፡፡ በጭንቅ እና በድንጋጤ ጊዜ በደመነፍስ የምናደርጋቸው ነገሮች ኋላ ላይ ያልፈለግነውን እና ያላስተዋልነውን ችግር ይዘውብን እንዳይመጡ አዕምሮአችንን አረጋግተን ፣ ነገሮችን በተለያየ መንገድ መዝነን እንከውን፡፡
  • ታማኝ የመረጃ ምንጮችን ብቻ እንጠቀም፡   ጭንቀት እና ድብርት የሚጨምሩ በኮቪድ-19 ዙሪያ የሚወጡ ዘገባዎችን መመልከት እና መስማት እንቀንስ ፤ ራስዎን እና ሌሎችን ከወረርሽኙ ለመጠበቅ ተግባራዊ እርምጃዎችን መውሰድ እንዲችሉ በዋናነት የታመኑ የመረጃ ምንጮችን ብቻ ይከታተሉ። 

መረጃዎችን በቀን ውስጥ በተወሰነ ሰዓት ፣ አንድ ወይም ሁለት ጊዜ ብቻ ይከታተሉ፡፡  ስለ ወረርሽኙ በየጊዜው የሚወጡ ድንገተኛ እና ተደጋጋሚ ዜና ዘገባዎች ማንኛውም ሰው በጭንቀት እንዲዋጥ ሊያደርጉ ይችላል። እውነተኛ ዜናዎችን ብቻ ይፈልጉ ፤ የግምት ወሬዎች እና የተሳሳቱ መረጃዎችን ያስወግዱ። የግምት ወሬዎችን እና የተሳሳቱ መረጃዎችን ከእውነተኛው ለመለየት እንዲረዳዎ ከዓለም የጤና ድርጅት ድረገፅ  እና ከአካባቢዎ/ሀገርዎ የጤና ሚኒስቴር ገፆች እና ሚዲያ በመደበኛነት መረጃዎችን ይመልከቱ፡፡ እውነተኛ ዜናዎች ፍርሃትን ለመቀነስ ይረዳሉና፡፡

  • ራሳችንን እየጠበቅን ሌሎችንም እንርዳ ፣ እናበርታ፡   ሌሎችን በችግራቸው ጊዜ መርዳት ፣ ድጋፍን መስጠት እና ማበረታታት  ደጋፊውንም ሆነ ርዳታ የሚያስፈልገውን ሰው ይጠቅማል፡፡ አንድ ሰው በጭንቅ ጊዜ ብቻውን እንዳልሆነ ማወቁ ከፍተኛ የሆነ አዕምሮአዊ ሰላምና ረፍትን ይሰጠዋልና፡፡ ለምሳሌ፡ ስልክ በመደወል ፣ በተለያዩ የማህበራዊ ትስስር መድረኮች በማዋራት ቤተሰቦቻችንን ፣ ጓደኞቻችንን ፣ ወይም የሚመስሉንን የማህበረሰብ ክፍሎች አለን በማለት ብቻቸውን እንዳልሆኑ ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ እንደ አንድ ማህበረሰብ አብሮ መሥራት COVID-19 ን በጋራ ለመከላከል እና አንድነትን ለመፍጠር ይረዳል ፡፡
  • ማህበራዊ ትስስርዎን አያቋርጡ ፤ መልካም የሆኑ ፣ ሌሎችን ባሉበት ሆነው የሚያሳትፉ ፣ የሚያስተምሩ እና የሚያዝናኑ ጨዋታዎችን ይፍጠሩ / ይሳተፉ፡  ማህበራዊ ትስስር ገፆችን እንጠቀምባቸው፡፡ ወቅታዊ እና ዕውነተኛ መረጃዎችን ከማግኘት ባለፈ ፣ ፈታ የሚያደርጉ ፣ አዳዲስ ነገሮችን የሚያሳውቁን ፣ አልፎም ሰውኛ የሆኑ ጨዋታዎችን በመፍጠር ፣ ወይም በመሳተፍ ትርፍ ጊዜዎን ያሳልፉ፡፡ በኢንተርኔት ከሚመጡ አደጋዎች ራስዎን መጠበቅን ግን አይርሱ፡፡
  • ያንብቡ፡   “መፃሕፍት እንዲህ ናቸው፡፡ እግርዎን ሳያንቀሳቅሱ እንዲጓዙ ያደርጉዎታል፡፡” “That’s the thing about books. They let you travel without moving your feet.” ~ Jhumpa Lahiri.
  • በዚህ ወቅት ለሚሰሙዎት ስሜቶች እና ፍላጎቶች ትኩረት ይስጡ፡፡ ጤናማ እና የሚያዝናኑ ፣ የሚደሰቱባቸውን ነገሮች ያድርጉ፡፡ መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ልምድን ያዳብሩ ፣ መደበኛ የሆነ የእንቅልፍ ሰዓት ይኑርዎት ፣ ጤናማ አመጋገብ ይኑርዎት፡፡
  • ሁልጊዜ ማድረግ ፈልገው በጊዜ ማጣት ምክንያት ሊያደርጓቸው ያልቻሏቸውን ነገሮች ያድርጉ፡፡ አዳዲስ ፈጠራዎችን ይማሩ ፣ የቤት ውስጥ ስራዎትን የሚያቀላጥፉልዎትን መንገዶች ይፍጠሩ፡፡ ቤትዎትን ያፅዱ ፣ የቤት ዕቃዎችዎትን አቀማመጥ ወይም ቦታቸውን ያቀያይሩ ፣ ቤትዎን በቻሉት አቅም ያስውቡ ፤ ምግብ ያብስሉ ፣ ራስዎን በሥራ ይጥመዱ፡፡
  • በመጨረሻም የጭንቀት ፣ ወይም ከፍተኛ የሆነ የድብርት ስሜት ሲሰማዎት የቅርብዎ የሆነን ሰው ያውሩ፡፡ ከተቻለም የአዕምሮ ጤና ባለሞያን ያማክሩ፡፡

ራሳችንን እየጠበቅን ሌሎችንም እንጠብቅ ፣ እናበርታ!

©የዜግነት ክብር ፡ መጋቢት 2012

Picture credit: monthlyreview.org