የተመሳሳይ ፆታ ተማርኮ እና Covid-19 ምን አገናኛቸው?
Covid-19 (ኮሮና ቫይረስ) ከምን መጣ? የሌሊት ወፍ ፣ እባብ ፣ ወይም ሌላ እንስሳ በመመገብ? ወይስ በላቦራቶሪ የተፈበረከ ምስጢር? ወይስ ደግሞ እንደ አንዳንድ የኃይማኖት እና የባህል አምባሳደሮች አስተያየት ለ”ኃጥያት” እና “በደል” ምላሽ ከላይ የተላከ የፈጣሪ ቁጣ?
እውነት ለመናገር መልሱ ቁልጭ ብሎ የተቀመጠ ነገር አይደለም፡፡ በመነሾው ዙሪያ የሚታገሉት ሳይንቲስቶችም ይህ ልዩ የሆነ ቫይረስ እንዴት እንደሚዛመት ፣ ወይም እንዴት መከላከል እንደሚቻል በእርግጠኝነት ለመናገር አጥንተው አልጨረሱትም ፤ እሰከ አሁን ድረስ ፍለጋ ላይ ናቸው፡፡
ሰሞኑን በተለያዩ ፣ በተለይም ኑሮአቸውን ከኃይማኖት ጋር አቆራኝተው የሚመሩ ህዝቦች ባሉባቸው ሀገራት የሚገኙ የኃይማኖት መሪዎች እና ሌሎችም የቫይረሱን መነሻ ከተመሳሳይ ፆታ ፍቅር ጋር አቆራኝተው ፈጣሪ በምላሹ የላከብን ቁጣ እንደሆነ በተደጋጋሚ እየተናገሩ ይገኛሉ፡፡ የፈለጉትን የማመን መብታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ፣ ነገር ግን ይህ ተደጋጋሚ አስተያየታቸው ከቫይረሱ በተጨማሪ በተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ የሚነሳ ጥቃትና አመፅ መንስዔም መሆን ጀምሯል፡፡
አንድ በማሌዥያውያን ዘንድ በብዛት .. እስከ 20 ሺህ ጊዜ.. የተሰራጨ የፌስቡክ ፖስት አሁን በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በሰፊው እየተጠቁ ያሉት ሀገራት ለምን ይህ እንደደረሰባቸው ለመተንተን ሲሞክር፡ ቻይና ውስጥ ሙስሊሞችን እና የአንዳንድ እንስሳት መገደልን እንደምክንያት ያስቀምጣል፡፡ ጣልያን ውስጥ የሚካሄዱ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ፌስቲቫሎች ለጣሊያን በበለጠ መጠቃት ምክንያት አድርጎታል፡፡ ኢራን ውስጥ ደግሞ የሱኒ ሙስሊሞች መገደል ላይ አሳብቦታል፡፡ በእነዚህ ምክንያቶችም ፈጣሪ እነዚህን ሀገራት በበለጠ ፣ ቀጥሎም ሌሎች የዓለም ሀገራት ላይ በትሩን እንዳሳረፈ ይናገራል፡፡ በተጨማሪም የትራነስጀንደር ሰዎች ወደ መካ የሚያደርጉት ጉዞ መጨመር ፣ ፈጣሪን ቫይረሱን ወደመካ በመላክ የማፅዳት ዘመቻ እንደጀመረ ይደመድማል፡፡
እንዲህ ዓይነት የተመሳሳይ ፆታ ተማርኮ እና ሌሎች ማንነቶች (SOGIE – Sexual Orientation and Gender Identity and Expression) ዓለም አቀፋዊ የሆኑ ተፈጥሮአዊም ሆኑ ሰው ሰራሽ ክስተቶች እና አደጋዎች ጋር መያያዛቸው አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ይህ የህብረተሰብ ክፍል ለጎርፍ ፣ ከባድ አውሎ ፣ ሰደድ እሳት እንዲሁም ለእንዲህ ዓይነት ወረርሽኞች መነሻ ተደርጎ ሲኮነን ኖሯል ፣ እየኖረም ነው፡፡
ወረርሽኙን ለመቋቋም ዓለም አቀፉን ትግል የሚመራው የዓለም ጤና ድርጅት ይህ የተሳሳተ መረጃ ማግለል እና መድልዎን ከማባባስ ፣ እንዲሁም ጥቃትን እና አመፅን ከማስፋፋት የዘለለ ጥቅም እንደሌለው በማስጠንቀቅ በቶሎ እንዲቆም ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
“በዚህ አዲስ ቫይረስ ምክንያት ከፍተኛ ፍርሃት በተንሰራፋበት በዚህ ወቅት እውነታውን ከሀሰተኛ መረጃዎች መለየት እና ማንኛውንም ዓይነት አግላይ ሃሳቦች አለመቀበል ይበልጥ አስፈላጊ ነው፡፡ “ ይላሉ የተባበሩት መንግስታት ደጋፊ ፋውንዴሽን ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ኬት ዶድሰን፡፡
በቻይና ውሃን ከተማ እንደተነሳ የሚታሰበው ኮሮናቫይረስ በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ ከ 2.5 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ያጠቃ ሲሆን ከ 178 ሺህ በላይ ሰዎችን ህይወታቸውን ቀጥፏል፡፡ ፡፡
የህክምና ባለሞያዎች በሽታው መጀመሪያ የሌሊት ወፍን ወይም ሌላ እንስሳን ያጠቃ ሲሆን ቀጥሎም ወደ ሰዎች እንደተዛመተ ያምናሉ፡፡ በእርግጠኝነት እንዴት እንደተላለፈ ግን እስካሁን ግልፅ አልሆነም፡፡
ሳይንቲስቶች እና የህክምና ባለሞያዎች መልሶችን ፍለጋ በሚፈልጉበት ጊዜ አንዳንድ የኃይማኖት ሰባኪዎች እና ሰዎች የራሳቸው ድምዳሜ ላይ በመድረስ ዜጎችን (የተመሳሳይ ፆታ ተማርኮ እና ሌሎች ማንነቶች) መውቀሱ ላይ አተኩረዋል፡፡
97 በመቶ ህዝቧ በኃይማኖት ህግጋቶች እና ሥርዓቶች የሚኖሩባት ሀገራችን ላይም ጉዳዩ የተለየ መልክ የለውም፡፡ ቀድሞ በነበረው የዜጎች ጥላቻ ላይ ይህ ወረርሽኝ ተጨማሪ ነዳጅ እየሆነ ያለበት ሁኔታ ይታያል፡፡ በተለያዩ ማህበራዊ ትስስር ገፆች እና መገናኛ ብዙሃን የዜጎች መበራከት ለወረርሽኙ መንስዔነት ፣ በተለያዩ የኃይማኖት ሰዎች እየታጨ ይገኛል፡፡ ይህ ሁኔታም ቀድሞውኑም በራስ መተማመኑ እና ራሱን መቀበሉ ጥያቄ ውስጥ ገብተውበት የነበረውን ዜጋ ወደበለጠ ጭንቀት እና ራስን የመጥላት ስሜት ውስጥ እየከተተው ይገኛል፡፡
በተለይም የኃይማኖቶች በመንግስት ደረጃ ተቀባይነት እያገኘ መምጣት እና ኃይማኖቶች መንግስታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ እየገቡ የባለቤትነት ስሜት ማሳደር ፣ ነገሩን እያባባሰው ከፍተኛ ፍርሃትን በዜጋው ዘንድ ፈጥሯል፡፡
አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያመለክቱትም ከሆነ ቫይረሱ በብዛት የተስፋፋባቸው አካባቢዎች ለመስፋፋቱ መጠን ማደግ ምክንያት ከሆኑ ነገሮች አንዱ በቤተክርስቲያን እና መስጊዶች የሚደረጉ ኃይማኖታዊ ስብሰባዎች እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ በሀገራችንም ያሉ ታላላቅ ኃይማኖቶች የሳይንስን ጥሪ ተቀብለው ቤቶቻቸውን ቢዘጉም ፣ ትክክለኛ መነሻ መንገዱ እና ፈውሱ እስኪገኝ ድረስ ከመጠበቅ ይልቅ መምህሮቻቸው እና ተከታዮቻቸው ፈጣሪ ስለዜጎች ብሎ ያመጣው ቁጣ እንደሆነ ደጋግመው ሲናገሩ ይስተዋላል፡፡
እንደ ግል አስተያየቴ፡ ይህ ዜጎች ላይ የሚደረግ ኩነና የቫይረሱን መነሻ ካለመረዳት እና በኃይማኖት ሥርዓቶች መፈወስ አለመቻሉን ለመሸፋፈን የሚደረግ ትግል እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ቁጣም ከሆነ እንደ ኃይማኖተኛ ወደራሳችን አይተን ሌሎች በጣም ብዙ “ኃጥያት” ተብለው የተቀመጡ ሥራዎች አሉንና እነሱንም ከግምት ውስጥ ማስገባት አለብን፡፡ ነገር ግን … አንዱ በሰራው ኃጥያት ሚሊዮን ሰዎችን የሚገድል ፈጣሪ ያለ አይመስለኝም፡፡ የሰው ልጅንም ዳግመኛ ላያጠፋ ቃል እንደገባ የሚያስተምር ኃይማኖት በእርግጥም የፈጣሪ ቁጣ ነው ብሎ የሚያምን አይመስለኝምና ይህንኑ የሀሰት መረጃ የሚበትኑ መምህራኑን እና ምዕመኑን አንድ ልጓም ሊያበጅላቸው ይገባል፡፡
ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የቫይረሱን መነሾም ሆነ መከላከያ መንገዱን የህክምና ባለሞያዎች እና ሳይንቲስቶች አጥንተው ባለመጨረሳቸው ይኼ ነው የሚባል ነገር የለውም፡፡ ከተጠቀሱት እንስሰዎች እንደተነሳ ቢታመንም እርግጥ ግን አይደለም፡፡
ቫይረሶች በባህሪያቸው በዘረመል ለውጥ (genetic mutation) ሳቢያ ከዝርያ ወደ ዝርያ የመሸጋገር ባህሪይ አላቸው፡፡ ባዮሎጂም የሚያረጋግጠው ሀቅ ነው፡፡ ታዲያ ለምን ይኼ ልዩ ቫይረስ ለመቆጣጠር አስቸገረ? ለምንስ እየተባባሰ መጣ? መልስ የምንጠብቅለት ጥያቄ ነው፡፡
አሁን ላይ የምናውቀው ቫይረሱ በንክኪ እና በሳል ፍንጣሪዎች አማካኝነት እንደሚተላለፍ ነው፡፡ አካላዊ ፈቀቅታም የመስፋፋት ኃይሉን ለመቆጣጠር የሚረዳን ዋነኛው መንገድ መሆኑን እናውቃለን – ባንተገብረውም፡፡ የጤና ሚኒስትሮቻችን እጆቻችንን በየጊዜው እንድንታጠብ ያስጠነቅቁናል – የግል ንፅህና ለዚህ ቫይረስ መዛመት መቋረጥ ቁልፍ እንደሆነ እናውቃለን ፤ ከቤት ውጪ ውለን ስንመለስ ወዲያው ልብሶቻችንን ማጠብ እና ማፅዳት እንዳለብን እንማራለን ፤ ነገር ግን ስንቶቻችን ነን የምንተገብረው?
እውነታው ይኼ ነው፡፡ ዜጎች የቫይረሱ መዛመት መነሻ እንደሆኑ መነገሩ ምንም ዓይነት አመክንዮአዊ ምክንያት የለውምና ሊታሰብበት ይገባል፡፡ በተገቢው አካላት የሚነገረንን ነገር አለመፈፀም እንጂ የተመሳሳይ ፆታ ተማርኮ ቫይረሱን አያዛምተውም፡፡
እኛም ይህንን ተረድተን ያለ ድንጋጤ እና ፍርሃት አካላዊ ፈቀቅታችንን እየጠበቅን ፣ በየጊዜው እጆቻችንን በመታጠብ ፣ ሌሎች ሊደረጉ የሚገባቸውን ነገሮች እየተከተልን ራሳችንንም ሌሎችንም እንድንከላከል አደራ እላለሁ፡፡
ቸር ያውለን!
©የዜግነት ክብር – ሚያዝያ 2012