ሰውነት

ሰው ነሽ! ሰው ነህ! ሰው ነኝ!

ሰው ናት! ሰው ነው! ሰው ናቸው! ሰው ነን!

ሰው ናችሁ!

….

አስተውላችሁ ከሆነ በዚች አጭር ፣ ነገር ግን ብዙ ፅሁፍ ውስጥ …. ነህ ፣ ነሽ ፣ ነን፣ ናችሁ… ሌሎችም፤ በሚባሉ የመለያ እና የመለያ (ሲጠብቅም ሲላላም) ብዝሃነት ውስጥ አንድ ነገር ብቻ ተደጋግሟል – ሰው!

ሰውነት ጥርስ ካላበቀለው ፣ የሌላ አዋቂ ሰው ክትትል ከሚያስፈልገው ጨቅላ እስከ ጥርሱን ካወለቀው ፣ በተመሳሳይ የሌላ አዋቂ ሰው ክትትል እስከሚያስፈልገው አዛውንት ፤

ሰውነት

ከጥቁሩ እስከ ነጩ ፣ ከአጭሩ እስከ ረጅሙ ፣ ከ “ቆንጆ”ው እስከ “መልከ ጥፉ”ው ፣ ከሴቱ እስከ ወንዱ እንዲሁም ፆታ አልባው ፣ ከሱሪ ለባሹ እስከ ቀሚስ ለባሹ እንዲሁም የፆታ ገደብ እስተሌለው ፣ ከተማረው እስከ አልተማረው ፣ ከ “ኃጢአተኛው”  እስከ “ፃድቁ” ፣ ከባለትዳሩ እስከ ላጤው ፣ ከቤት እመቤቱ እስከ ሴተኛ/ወንደኛ አዳሪው ፣ ከጤነኛው እስከ ጤና አልባው ፣ ከኃይማኖተኛው እስከ ኢ-አማኒው ፣ ከ… እስከ …. ድረስ በአንድነት አቆራኝቶ ፣ የጋራ ዕኩል ማንነት ሰጥቶ ፣ አንድ የሚያደርገን ህልውናችን ነው ፤ ሰውነት፡፡

አሁንም አስተውላችሁ ከሆነ ይህንኑ ሰውነት በተለያዩ መገለጫዎች እና ስያሜዎች ከፋፍለነዋል፡፡ እነዚህም አንዱን ከአንዱ ለመለየት የተጀመሩ መለያ ቃላት ወይም ሁናቴዎች ወደ ማህበረሰባዊ ህግጋትነት ቀይረናቸው እዚህ ደርሰናል፡፡

ሰው ግን ምንድን ነው?

እኔን ብትጠይቁኝ የማንንም ፈላስፋ ጥቅስ ጠቅሼ አላስረዳችሁም፤ ወይም የየትኛውንም ኃይማኖታዊ ፅሁፍ ተንተርሼ ሰውን አልገልጥላችሁም፡፡ የራሴን አመለካከት ብቻ ነው የማጋራችሁ፡፡ እርግጥ ነው በዘመኔ ያነበብኋቸው ፅሁፎች ፣ የተማርኳቸው ትምህርቶች ፣ ያገኘኋቸው ልምዶች አሁን ላለኝ የሰውነት አመለካከት ተፅዕኖ እንዳላቸው አልክድም፡፡ ግን ከእያንዳንዱ አንዳንድ… የሆነ የሆነ ነገር ወሰድኩ እንጂ ፣ ይኼ ብቻ ነው ትክክል ፣ ወይም ያኛው ነው ዕውነተኛው መንገድ ብዬ አንዱን ብቻ ነጥዬ ለመውሰድ ሰውነቴ አልፈቅድልህ አለኝና የራሴን መንገድ ይዤ ልጓዝ ወሰንሁ፡፡

ሰው ምንድን ነው?

ሰው ፍጡር ነው፡፡

ፍጡር ነው ያልሁበት ምክንያት እስካሁን የፈጣሪን መኖር ደግፈው የሚከራከሩት ፣ የፈጣሪን ህልውና እንዲሁም ፈጣሪን የሚያስረዱበት እና የሚገልጡበት መንገድ ባያሳምነኝም እና ባልስማማበትም ፣ ሰው በበኩሉ … በእኔ አመለካከት … ይህ መንገዱ ደካማነቱን ይበልጥ የሚያጋልጥበት መሆኑን ያለመረዳት ስንፍናው እና ጠባብነቱ … እውነትም ፍጡር ነው ስለሚያስብለኝ ነው፡፡ ቀላሏን ሀቅ … ሰውነትን … መረዳት አለመቻሉ መልስ ይሰጠኛል፡፡ ፍጡርነቱን፡፡

ሰው ፈጣሪ ነው (መለኮታዊ ነው)፡፡

ፈጣሪ ነው ያልኩበት ምክንያት ደግሞ፡ አብዛኛው ኃይማኖቶች የሚጋሩት ብዙ አይነት ነገር አለ፡፡ የዶግማቸው አወቃቀር ይለያይ ፣ የታሪካቸው ፍሰት ይራራቅ ፣ የገፀባህሪያቶቻቸው ስም እና ዘር ይለያይ እንጂ … ሁሉንም አንድ የሚያደርጋቸው አንድ ነገር አለ፡፡ ሁሉም አንድ ፈጣሪ ሰውን መፍጠሩን፡፡ አብዛኞቹ ኃያላን ኃይማኖቶች የሚጋሩት አንድ ሌላ ነገር ደግሞ አለ – ፈጣሩ በመልኩ ፣ በአምሳሉ ፣ በግብሩ ሰውን መፍጠሩን፡፡

ታዲያ ፈጣሪ ሰውን በአምሳሉ እና በግብሩ ከፈጠረው ሰው እንዴት ፈጣሪ አይደለም? እንዴት መለኮታዊ ባህሪይ የለውም… አለው እንጂ፡፡ ይህ ሁሉ ዕውቀት እና ጥበብ ከፈጣሪ የሚገኝ ከሆነ ፣ ፈጣሪ ከላይ ሆኖ የፈጠረውን ፍጡር ይገዛል ከሚለው ይልቅ … ፈጣሪ ራሱ በፈጠረው መንገድ (ሰውነት) ራሱን እየገለጠ መሆኑን ለመረዳ ትንሽ ስለሚቀልለኝ … ሰው ፈጣሪ ነው፡፡ በቀላሉ ሰው የፈጣሪ መገለጫ መንገድ ነው ለማለት ነው፡፡

የሁሉ ነገር አስገኚ አንድ ፈጣሪ ከሆነ ፣ የሰው ልጅም ዕውቀቱን ፣ ነገሮችን የመፍጠር ብቃቱን ፣ ማመዛዘኑን ፣ ማስተዋሉን ፣ መውደዱን ፣ መጥላቱን ፣ ስሜታዊነቱን … ሁሉንም ነገር ያገኘው ከፈጣሪ ነውና፡፡

ሰው ተፈጥሮ ነው፡፡

ወይም ደግሞ በራሴ አገላለፅ … ተፈጥሮ በተለያየ መንገድ ፣ በተለያየ ሁናቴ ራሷን ስትገልጥ ወይም ደግሞ ካለመኖር ወደመኖር ስትመጣ ፣ ከተገለጠችባቸው አንዱ ሰውነት ነበረና ሰው ከተፈጥሮ የተገኘ አንድ ቅንጣት ወይም መገለጫ ነው ማለት ነው፡፡ ሰው ተፈጥሮ ነው፡፡

ታዲያ ሰውን በተለያየ መንገድ እንግለፀው ፣ በተለያየ ቀለም ይገለጥ ፣ የተለያየ ስሜት ይኑረው ፣ የተለያየ ነገር ያምልክ እንጂ… ሰው አንድ ነው፡፡

ሰውነትን የምረዳበትን አንዳንድ በጣም ቀላል እና ቂላቂል የሚመስሉ ነገር ግን ለእኔ ብዙ ትርጉም ያላቸውን  ምሳሌዎች ልንገራችሁ፡፡

የሰው ልጅ አካባቢውን አሸንፎ ፣ ከሌሎች የተፈጥሮ መገለጫዎች በሙሉ ልቆ ፣ የማሰብ ነፃነቱን ተጠቅሞ ተፈጥሮአዊ ልዕልናን የተጎናፀፈበት መንገድ በሁሉም ሰው በሚኝበት አካባቢ ተመሳሳይ ነው፡፡

አንዲት በኢትዮጵያ ገጠራማ ቦታ የምትገኝ ድሃ ባልቴት እና በጃፓን ከሚገኙ ድሃ መንደሮች ውስጥ በአንዱ የምትገኝ እናት ኑሮአቸውን ለማሸነፍ በሚያደርጉት ትግል የሚፈጥሯቸው ዘዴዎች ፣ የሚጠቀሟቸው ነገሮች ፣ የሚሰሟቸው ስሜቶች ፣ የሚወስኗቸው ውሳኔዎች ሁሉ … እንደየባህላቸው ይለያዩ እንጂ በእጅጉ ተመሳሳይ ናቸው፡፡

በአንድ የዓለማችን ቀዝቃዛ ቦታ ላይ የሚገኝ ገበሬ እና በሌላኛው የዓለም ቀዝቃዛ ቦታ ላይ የሚገኝ ገበሬ ፣ በተለያየ ቦታ ላይ ቢገኙም ተመሳሳዩን ተፈጥሮአዊ የአየር ፀባይ የሚቋቋሙበት መንገድ እና ኑሮአቸውን የሚመሩበት ሂደት በጣም ተመሳሳይ ነው፡፡

እስቲ… የማንተዋወቅ ሰዎች ለራሳችሁ ይሄን ጥያቄ መልሱልኝ፡፡ ጥርሳችሁን ስትቦርሹሹ.. ቡሩሹን ወደ ጉሮሮአችሁ ስታስጠጉት… ቋቅ አይላችሁም? (ቪክተር ጌታ – ይኼ ጥያቄ አንተን አይመለከትም ፡) ) … መልካም ነገር ስታዩ መንፈሳችሁ አይደሰትም? መጥፎስ ነገር ስታዩ አይከፋችሁም? አትናደዱም? ፣ አትወዱም? አትጠሉም? አትቀኑም? አትናፍቁም? አታዝኑም? አትደሰቱም?

ለራሳችን ጥኑ ነገርን አንመኝም? እንመኛለን አይደል? … በቃ… ሌላውም ሰው ልክ እንደ እኛ ለራሱ ጥሩ ነገርን እንደሚመኝ መረዳትን ነው ሰውነት የምለው፡፡ እነዚህ ቀላል ሰዋዊ የሆኑ ስሜቶቻችን አንድ ያደርጉናል፡፡ በተለያየ መንገድ ብንገልጣቸውም፡፡

እና በግል አስተያየቴ… ሰውነትን እንዲህ ቅልል ባለ መልኩ ፣ ራሳችንን በማየት ብቻ አለመረዳታችን ይመስለኛል ከከበርንበት መለኮታዊ ማንነታችን አውርዶ ጥላቻ የሚባል ነገር እንድንፈጥር ያስገደደን፡፡ እንጂማ በሰይጣኑስ ለምን ይላከካል?

እውነቱን እንነጋገር ከተባለ እርሱስ ቢሆን (ሰይጤ) የኛው ፈጣሪ ፍጡር አይደለምን? ፍጥረቱ እንዲያገለግለው ከፈጠረው ደግሞ …ሁሉ ፍጡር አገልጋይ ነውና … ሰይጣንዬም በፍጡርነቱ የተጣለበትን የሥራ ግዴታ እየተወጣ ያለ ፣ እንደኛው ለፈጣሪው የሚገዛ አገልጋይ ፣ ፍጡር ነው፡፡ ይመስለኛል፡፡ (እብድ ነህ በሉኝ)

ዕውነት ለመናገር ከምወደው ሰውኛ ባህሪዬ … ፈጣሪ አለ ብዬ እንደማምን አንድ ሰው … ህልውናውን በራሴ መንገድ ለመረዳት እና ለማድነቅም ሆነ ለመኮነን በራሴ የኃሳብ ባህር ውስጥ የምንቦጫረቀው ነገር ነው፡፡ (እርግጠኛ ነኝ ፣ አምነን ለመቀበል ብናገራግርም በሁሉም ሰው ዘንድ ያለ ያልተፈታ ምስጢር ነው – የህልውናው ነገር፡፡) እና ብዙም አትኮንኑኝ… ሰውኛ ባህሪዬ ነውና … ለማለት ነው፡፡

ሌላ ጊዜ ልመለስበት? ፍቀዱልኝ….

ቤን ዶሚነስ ነኝ

በዕውቀት የዜግነታችንን ክብር እንጎናፀፋለን!
#ዜጋ #ዕውቀት #መዝናኛ #የዜግነትክብር #ሰው #ታሪክ #ማንነት