ሴት የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ | Lesbian

ወቅቱን አሁን በውል ባላስታውሰውም ፣ የሆነ ጊዜ ላይ ከአንድ የተቃራኒ ፆታ አፍቃሪ (ቀጥ) የሆነ የሥራ ባልደረባዬ ጋር ስለ ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን (ዜግነት) የተለመደውን ኃጥያት ነው ፣ አይደለም ክርክር ገጥመን ነበር፡፡ የባልደረባዬ የመከራከሪያ ኃሳብ ከኃጥያትነት በዘለለ የሰው ልጅ ተፈጥሮ ዋና ዓላማ ዘር ለመተካት በመሆኑ በሁለት ወንዶች መካከል የሚደረግ ወሲብ ኢ-ተፈጥሮአዊ እንደሆነና ለተለያዩ የጤና እክሎች እንደሚያጋልጥ የሚተነትን ነበር፡፡

ይህ ባልደረባዬ ግን በሁለት ሴቶች መካከል የሚኖርን ስሜታዊም ሆነ ወሲባዊ ቅርርብ ወይም ግንኙነትን በፅኑ ይደግፋል – የራሱን የተቃራኒ ፆታ ወሲባዊ ጥማት ስለሚያስታግስለት፡፡ ይህ የባልደረባዬ ዕይታ የእርሱ ብቻ አይደለም፡፡ ብዙዎች የሚጋሩት እንጂ፡፡

የሴት ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን (ሌዝቢያን) በተለያዩ የተመሳሳይ ፆታ ፍቅር ተቃዋሚ አቀንቃኝ ሰዎች (በተለይም ወንዶች) ይህንን ወሲባዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ሲባል ብቻ ትኩረት የሚሰጠው በሁለተኛ ደረጃ ኃጥያትነት ነው፡፡ ምንም እንኳን የተመሳሳይ ፆታ ተማርኮ እና ሌሎች ማንነቶች የመብት ጥያቄዎች ላይ ሌዝቢያን ሴቶች በግንባር ቀደምትነት የሚገኙ ቢሆንም ፣ በአብዛኛው ህዝብ ላይ ያለው የአባታዊ ሥርዓት ተፅዕኖ ሴቶችን ከወሲብ ማርኪያነት እና ልጅ ፈልፋይነት በዘለለ ትኩረት ሳይሰጣቸው እንደነገሩ ይታለፋሉ፡፡

ይህ ሳምንት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሌዝቢያን ሴቶች ዕውቅና መስጫ ሳምንት (Lesbians Visibility Week) በመባል ታስቦ ይከርማል፡፡ ታዲያ ዛሬ ከላይ የጠቀስኩትን እና ሌሎች ሴት የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን (ሌዝቢያን) ላይ ያሉ እጅግ የተሳሳቱ ግንዛቤዎችን በጥቂቱ እናውራባቸው እስቲ፡፡

  • ሌዝቢያኖች ወንዶችን ይጠላሉ፡

የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ሴቶች (ሌዝቢያኖች) በፆታ ከሚመስላቸው ጋር በፍቅር ስለወደቁ ብቻ ተቃራኒያቸውን ይጠላሉ ማለት መሰረት አልባ ግንዛቤ ነው፡፡ እንደማንኛውም ሰው የሚወዷቸው አሳዳጊ አባት ፣ መካሪ ወንድም ፣ አስቂኝ አጎት ፣ ታማኝ ጓደኛ አላቸው፡፡ እርግጥ ነው በሁለት ተመሳሳይ ፆታ ባላቸው ሰዎች መካከል ተፈጥሮአዊ የሆነ ልዩ ቁርኝት አለ፡፡ ያ ማለት ግን ሌሎችን ስለጠሉ ነው ማለት አይደለም፡፡

እንዲያውም እኔ እንኳን በግሌ የማውቃቸው ሌዝቢያኖች ብዙ የወንድ ጓደኞች አሏቸው – ቀጥም ይሁን ዜጋ፡፡ እናም ቀጦችዬ … ጠልተዋችሁ አይደለም፤ አብረዋችሁ መተኛት ብቻ ነው የማይፈልጉት፡፡ ብዙ ልዩ የመሆን ስሜት አይሰማችሁ፡፡ ልክ እንደማንኛውም ሰው ለእነሱ እኩል ሰው ናችሁ፡፡

  • ሌዝቢያኖች በወንድ ስለተጎዱ ፣ ወይም እድገታቸው ላይ በአባታቸው/በወንድማቸው/በአጎታቸው ስለተደፈሩ ወይም ስለተጠቁ….

አትጨርሱት፡፡ አንዲትን ቀጥ ሴት ሄዳችሁ ቀጥ የሆነችው በሴት ስለተጎዳች ፣ ወይም በእድገቷ በእናቷ ፣ በእህቷ ወይም በአክስቷ ስለተደፈረች ወይም ስለተጠቃች ወንድ አፍቃሪ መሆኗን ትጠይቃላችሁ?  … አትጠይቁም፡፡

በዚህ ዕምነት … እያንዳንዷ በልጅነቷ ፣ በትምህርት ቤት ፣ በቤተሰብ አባል ፣ በመንገድ ዱርዬ ፣ እንዲሁም በእናንተ የተጠቃች ሁሉ ሌዝቢያን ናት ማለት ነው?  

ትናንትና መንገድ ላይ ዱርዬ ለክፏት እያለቀሰች ቤት የገባች ታናሽ እህትህ ሌዝቢያን ናት ብለህ ታምናለህ ማለት ነው?

ቀጦች ሆይ…. እመኑኝ … ሁሉም ነገር በእናንተ ዙሪያ አይሽከረከርም፡፡ የሷ ፆታዊ ተማርኮ የራሷ ነው፡፡ ከናንተ ወንድነት ጋር ቅንጣት ታህል ቁርኝት የለውም፡፡

  • በሌዝቢያኖች የፍቅር ግንኙነት ውስጥ ማነው ወንዱ ፣ ማናት ሴቷ?

ማንም፡፡

የሴት እና የሴት የፍቅር ግንኙነት  …  እዚህ አረፍተ ነገር ውስጥ ወንድ የሚባል ነገር ይታያል? … አይታይም፡፡ ፍቅር በሁለት ሰዎች …. (ሰዎች ነው ያልኩት … ወንድ ወይም ሴት አላልኩም) መካከል የሚኖር መጣጣም እና መግባባት እንጂ አንዳቸው መሪ አንዳቸው ተመሪ የሚሆኑበት ፣ አንዳቸው አስተዳዳሪ ሌላቸው ተዳዳሪ የሚሆኑበት … ያንን የተለመደውን አባታዊ ሥርዓት አይከተልም፡፡

ድጋሚ ቀጦች ሆይ…. እመኑኝ … ሁሉም ነገር በእናንተ ዙሪያ አይሽከረከርም፡፡ የሷ ፆታዊ ተማርኮ የራሷ ነው፡፡ ከናንተ ወንድነት ጋር ቅንጣት ታህል ቁርኝት የለውም፡፡

  • ሁሉም ሌዝቢያኖች ወንዳወንድ ናቸው

አሁንም ወንዶች ሆይ…. ምነው ሁሉ ነገር ከኛ ጋር ካልተቆራኘ አላችሁሳ? ወንዳወንድነት እና ሴታሴትነት ከፆታዊ ተማርኮ ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም፡፡ ወንዳወንድም ፣ ሴታሴትም … ወይም የሁለቱም ቅይጥ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ካልተነገራችሁ አታውቁም፡፡

ብቻ አንዲት “ወንዳወንድ” ሴት አይታችሁ …በድፍረት  “ሊሊ ነሽ ኣ!?” ብላችሁ ደም በደም አድርጋ እንዳትመልሳችሁ ተጠንቀቁ፡፡ ሃሃ

  • ወንድ ውቃቢ ያደረባት ሴት … ውቃቢዋ ሴት ስለሚፈልግ…..

በሉ… ይኼንን ባለውቃቢ ይመልስልኝ፡፡

እናላችሁ ሴቶችዬ … ዜጎችዬ … ሌዝቢያኖችዬ … ሴት የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያንዬ … ሊሊዎችዬ … ምንም እያሉ ቢጠሯችሁ … ምንም ቢሏችሁ …..

እኛ ግን ማንነታችሁ ዕውነት ፣ ፍቅራችሁም ንፁህ ፣ ቅርበታችሁም ከልብ እንደሆነ እናውቃለን!

ክበሩልን!!!!

©የዜግነት ክብር | ሚያዝያ 2012