ቡና ከቪክተር ጌታ ጋር – ክፍል አንድ

ቪክተር ጌታ ማነው?

አብዛኞቻችሁ ታውቁታላችሁ – በተለይም ፌስቡክ የምታዘወትሩ ከሆነ፤ ቧልተኛ እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ … በቅርበት የምናውቀው ደግሞ በቧልቱ ውስጥ የሚያስተላልፋቸውን ቁምነገሮች እናውቃቸዋለን፡፡

ብዙም አላስተዋውቀውም … እግር ጥሎን አግኝቼው ብዙ አውርተን ነበር ፤ በጣም ብዙ፡፡ በአንድ ወይም በሁለት ክፍል ብቻ አያልቅምና ዛሬ እንደነገሩ ልጀምርላችሁ፡፡ በሚቀጥሉት ቀናት ደግሞ ከተመቻችሁ ቀሪውን እቦጭቅላችኋለሁ፡፡


ቤን፡  እሺ ቪክቶር ጌታ …. እንዴት ነህ?

ቪክ፡  ይቅርታ … ቪክተር ነው!

ቤን፡  አዪዪዪ… በቃ ልንከርም ነው እንዲህ ስንተራረም

ቪክ፡   ስሜን አስተካክለህ ጥራኣ ታዲያ!

ቤን፡  እሺ … ቪ ክ ተ ር ጌታ! … ፈቃደኛ ስለሆንክ አመሰግናለሁ! … ቀድሜ አንዳንድ ነገሮችን ልንገርህ … ስለማላምንህ፤ ሃሃ… መናገር የማትፈልገውን ነገር ከተናገርክ … እንድሰርዘው ንገረኝ፤ ያወራነውን እንዳለ… እንደወረደ ስለማሰፍረው፡፡

ቪክ፡  ችግር የለም፤ ፕሩፍ ሪድ ግን አደርገዋለሁ አይደል?

ቤን፡  ለምን ለምርጫ አትወዳደርም?

ቪክ፡  ሃሃሃሃሃ …. ምልክቴ ቁላ ነው!

ቤን፡  ውድ አንባቢዎቼ!…. ዕድሜአቸው ለዓቅመ ቪክተር ያልደረሱ እንዲያነቡት አይመከርም!

ቪክ፡  እንዲያውም ሰርፕራይዝ አድርገኝ! … ፈረንጆቹ እንደሚሉት እኔ Open Book ነኝ!

ቤን፡  የዱሮዋ በላይ ዘለቀ … የአሁኑ ቪክተር ጌታ…

ቪክ፡  እሺ ዴመን ሹሉቃ!

ቤን፡  ሃሃሃሃሃ…. ያኔ ትዝ ይለኛል …. በጣም ፌመስ ነበርክ፡፡ ካማል ፍፁም አድ አድርገው ብሎኝ … ልኬልህ፡ ጥያቄዬን እስክትቀበል ድረስ በቃ …. የሆንክ ቁንን ያልክ ነበር የምትመስለኝ፡፡ ሃሃሃ

ቪክ፡  እንዴ ኧረ እኔ ወዲያው ነው የምቀበለው!! ሃሃ

ቤን፡  ሃሃ…. እና እንዴት ነህ? … ህይወት እንዴት ነው? …

ቪክ፡  ደህና ነኝ! ምንም አልል፡፡

ቤን፡  ኮሮናስ እንዴት እያደረገህ ነው?

ቪክ፡  ወይኔ ኮሮና ፡ ይኸው እቤቴ ከተቀረቀርኩ ሦስት ሳምንቴ፤ ለአንዳንድ ሥራዎች ብቻ ነው እንጂ

ቤን፡  እና ዛሬ ለኔ ቡና ስትል ነው የመጣኸው?

ቪክ፡  ይኸው ላጣጣህ ብዬ … ስንት ሀገር አቋርጬ … ስንት ሰዓት ፈጅቶብኝ…

ቤን፡  ኧረ በቃህ! .. ትረካ አስመሰልከው፡፡ ሃሃሃ ….

ቤን፡ እሺ … ታክሲ እንዴት ነበር ከተማው?

ቪክ፡  እንዴዴዴ…. ምንድነው ልትጠይቀኝ የቀጠርከኝ! ሥንት ስራ ፈትቼ እኮ ነው የመጣሁት!

ቤን፡  ሃሃሃ… እሺ መጀመሪያ መጠየቅ የምፈልገውን ልጠይቅህ… እ…

ቪክ፡  አዎ ሲንግል ነኝ!

ቤን፡  ሃሃሃሃ …. ወይ መከራዬ ዘንድሮ!

ቪክ፡  ሃሃሃ… እና ስትንተባተብብኝ ነዋ… እኔው ላጫውትህ እንጂ

ቤን፡  ሎል! … እሺ …. ሶሻል ሚዲያ ላይ በጣም አለህ! በተለይ ፌስቡክ ላይ … ዞር ስንል ቪክተር ነው … አንድ ግሩፕ ብንገባ .. ቪክተር ሲርገበገብ ነው የምናገኘው … ሌላ ግሩፕ ብንሄድ … ቪክተር ወንዶቹን ሲያንጫጫ ነው የምናየው ….

ቪክ፡  አዎ! … ላይፍ ስለሌለኝ ነው!

ቤን፡  ሃሃሃ. .. አንተ ልጅ ኧረ ተው! … ዛሬ ይኼን ነገር የምንጨርስ አይመስለኝም

ቪክ፡  ሃሃሃ…. እሺ ቀጥል

ቤን፡  ሆ! … እሺ ስለ ማህበራዊ ትስስር ገፆች … ወይም ሶሻል ሚዲያ ያለህን ሀሰብ እስቲ ንገረኝ፡፡ ደጋግሜ ነግሬሃለሁ መሰለኝ … በእኛ በዜጎቹ በኩል ብቻ ሳይሆን ፣ ቪክተር ጌታ … የቀጥ ተብለው በሚታሰቡት ገፆች ላይም ታዋቂ ነህ፡፡ እውነት ለመናገር … በእነዚህ ገፆች ላይ ያለህ ግልፅ የሆነ ተሳትፎ … በሆነ መልኩ ነገሮችን .. በተለይም የተመሳሳይ ፆታ ፍቅርን ኖርማላይዝ ያደረገባቸውን ቁጥር ያላቸውን አጋጣሚዎች አይቻለሁ፡፡ ፎቶህ ነው እንጂ የሌለው … ፌስቡክህ ለቀጡም ለዜጋውም አንድ አይነት ነው ፤ አንተነትህን እና ማንነትህን አትደብቀውም፡፡  እና… ግንዛቤን በመፍጠሩ ረገድ የራስህን የሆነ አስተዋፅዖ እየተጫወትክ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ … ስንት የኮመንት ጦርነት ውስጥ የከተትካቸው ፀረ-ተመሳሳይ ፆታ ተማርኮ ሰዎች … ዞረው ዞረው ጓደኛ ሆነውህ …ስትቀላለዱ ትታያላችሁ፡፡ … እስቲ አጫውተኝ …. ስላለው አጠቃላይ ሁኔታ

ቪክ፡  እኔንጃ…. ሲጀመር ያለሁት ፌስቡክ ላይ ብቻ ነው፡፡ ለዛም ይሆናል … ሙሉ ትኩረቴን ስለምሰጠው ይመስለኛል፡፡ ሲቀጥል ደግሞ ማንም የፈለገውን ሆሞፎቢክ ወይም ጥላቻ ያለው… የሆነ ነገር ሲናገር የምበሳጭበት እና የምናደድበትን ዕድሜዬን አልፌዋለሁ መሰለኝ … ብዙ አያስጨንቀኝም ፤ ቀልጄበት የሆነ ነገር ብነግራቸው እመርጣለሁ፡፡ እኔም ራሴን ለመቀበል የወሰደብኝን ጊዜ ስለማውቀው … ምናልባት እነዚህ ሰዎች ሌላ ዜጋ የሆነ ሰው አያውቁ ይሆናል ፤ እንደገና ደግሞ…እነዚህ ገፆች ላይ የዜጋ የሆነ ነገር ብዙም ያልለመዱ ወይም በጭራሽ ያላዩ ሰዎች ይሆናሉ… እና ዜጋ ነክ የሆኑ ነገሮች በብዛት ፖስት ሳደርግ ሊሳደቡ ምናምን እንደሚችሉ ቀድሜ ስለማውቅ … ብናገራቸውም በቀልድ መልክ ተናግሬ አልፈው ይሆናል እንጂ… ያን ያህል ሲሪየስ አድርጌ አልወስደውም፡፡ አልሸሻቸውምም …. በተጨማሪም … የሆነ ግሩፕ ላይ በጣም የጥላቻ ፖስቶች ቢበዙም … ከግሩፑ አልወጣም .. ወይም ብሎክ አላደርጋቸውም …

ቤን፡  ከተባረርክባቸው ግሩፖች ውጪ…. ሃሃ

ቪክ፡  እንዴ… የት ተባረርኩ!? የትም አልተባረርኩም …. እርግጥ የወጣሁባቸው ግሩፖች አሉ፤ ግን የምወጣው ችግሩ ከአድሚኖቹ ከሆነ ነው … የዜጋ ነገር ፖስት ሲደረግ አድሚኖቹ ከሆነ የሚንጫጩት እወጣለሁ፡፡ ከአባላቱ ከሆነ ግን አልወጣም፡፡ ሃሃ

ቤን፡  ቀጥ አድርገህ ትከላከላለህ

ቪክ፡  አዎ! … ቢያንስ የኛን ወገን ታሪክ … እንዲህ ነው እንዲያ ነው እያልኩ እመልሳለሁ፡፡ ሲጀመር ደግሞ…. የዜጋ ጉዳዮች ላይ ብቻ አይደለም የምሳተፈው እና የምወያየው … ሌሎች ጉዳዮችም ላይ በእኩል ደረጃ እሳተፋለሁ፡፡ የሴትና የወንድ ቀልድም ቢሆን አብሬ እቀልዳለሁ … ከዛ የራሴን ጣል አደርግበታለሁ.. ሃሃ፡፡

ቤን፡  እውነት ነው! … አሁን ለምሳሌ እኔ በእርግጠኝነት የማውቃቸው ፣ ሆሞፎቢክ የሆኑ ቀጦች በገፆቻቸው ላይ ፀረ-ዜጋ ጥላቻን የሚለጥፉ ምናምን … አንዳንዴ አንተንም ታግ እያደረጉ ሲፖስቱ አያለሁ፡፡ እና… አንዳንዴ ይገርሙኛል …ሳያውቁት ቀርተው ነው? ወይስ … ፕሮፋይሉን ሳያዩት ቀርተው ነው? …  እያልኩ ሁሉ እስቃለሁ፡፡

ቪክ፡  ሃሃ! … አዎ!  ብዙ ሰዎች አሉ… እንዲያውም አንድ ጊዜ የሆነ ፖስት ስር ስንከራከር … አንዱ … ዜጋ የሚመስሉ ሰዎችን እየዞርኩ እደበድባለሁ … እኔንም ፈልጌ እደበድብሃለሁ ፣ አርድሃለሁ ምናምን ሲል የነበረ ልጅ … ፍሬንድ ሪኩዌስት ልኮልኝ … አሁን ድረስ እናወራለን፡፡ ለበዓል ራሱ እንኳን አደረሰህ እንባባላለን ፤ ሃሃሃሃ ፡፡ ያኔ ግን… ካስታወስከው እዛ ፖስት ስር ከነበረው ንዴትና ክርክር … በዛን ጊዜ አግኝቶኝ ቢሆን ይሄኔ ገድሎኝም ይሆናል … ማን ያውቃል! ሃሃ … ብዙ ጓደኞች አሉኝ!

ቤን፡  መንገድ ላይ ምናምን ሰው ለይቶህ ያውቃል?

ቪክ፡  አዎ!

ቤን፡  የምር?

ቪክ፡  ምን ጋዜጠኛ ጋዜጠኛ ያጫውትሃል!? ታውቅ የለ እንዴ?

ቤን፡  እህህህ …

ቪክ፡  በአካል አይተውኝ ቪክተር መሆኔን ያወቁ … ሁለት ሰዎች ነበሩ፡፡ አንደኛው በቅርብ ነበር … ሰው ነግሮት ነው፡፡ ቪክተር እሱ ነው ተብሎ … መጥቶ ቪክተር ብሎ ሲጠራኝ … እኔም ከቀልቤ አልነበርኩም … አቤት! ማለት! … ከዛ ዞር ስል የማላውቀው ሰው ነው፡ ደንግጬ የታባቴ ልግባ!? ከዛ ግን … ማነህ ብዬ አዋራሁት … ለካ ፌስቡክ ላይ ጓደኛሞች ነን፡፡

ቤን፡  ዜጋ ነበር ግን?

ቪክ፡  አይደለም… ቀጥ ነው፡፡

ቪክ፡  ሌላ አንዲት ልጅ ደግሞ ካፌ ውስጥ አይታኝ ‘እዚህ ካፌ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ልብስ ለብሰህ አይቼሃለሁ!’ ብላ ቴክስት ላከችልኝ፡፡ እሷ ደግሞ ያወቀችኝ በቀለበቶቼ ነበር፡፡ አሁን ነው የቀነስኩት እንጂ በፊት ብዙ ቀለበት አደርግ ነበር፡፡ ከዛ በኋላ ግን በአካል ተገናኘን ፤ እንዲያውም በአካል ያወቅኋት የመጀመሪያዋ ቀጥ ሰው እሷ ነበረች፡፡ አሁንም ጓደኛሞች ነን … የኔንም ጓደኞች ተዋውቃለች፡፡

ቤን፡  ሶሻል ሚዲያ ላይ ብቻ አይደለም ለነገሩ ፤ አንተ ላይ አንድ ነገር ምን አስተውያለሁ መሰለህ፡ ብዙዎቻችን ከዜጋ ጓደኞቻችን ጋር ስንሆን እና ከቀጥ ጓደኞቻችን ጋር ስንሆን የተለያየ ዓይነት አቀራረብ እና ማንነት ይዘን ለመታየት እንሞክራለን፡፡ አንተ ላይ ግን ያንን አላይም …. ራስህን ስትቆጥበው ወይም ስትገድበው አላይህም… አንድ ቢሮም አብረን ሰርተናል … ያው ነህ

ቪክ፡  እና ፋጤሽን አትሰበስቢም እያልከኝ ነው!?

ቤን፡  ሃሃሃሃ … አዎ! አትሰበስብም!

ቪክ፡  እኔ እኮ የሰበሰብኩ ፣ የተረጋጋሁ ነው የሚመስለኝ

ቤን፡  ሃሃሃሃ

ቪክ፡  አስተዳደጌ መሰለኝ፡፡ ከቤት ሳልወጣ ፣ ጥብቅ ቤተሰብ ጋር ነው ያደግሁት፡፡ ከቤት ውጪ ፣ ሰፈር ውስጥ ያለውን የአካባቢ ተፅዕኖ አላውቀውም ነበር፡፡ ከሦስት ልጆች ውስጥ ሁለተኛው ነኝ … እና እንዲህ ሁን ፣ እንዲህ መሆን አለብህ … እየተባልን አይደለም ያደግነው፡፡ ልጅም እያለሁ እንዲሁ ነኝ .. ከነፋጤዬ፤ ትምህርት ቤት ስገባ ነው ግራ የገባኝ፡፡ ነፃ ሆኜ ስላደግሁኝ ይሄንን ባህሪዬን መደበቅ እንዳለብኝ ፣ ወይም በሌሎች ሰዎች ዘንድ እንደ “መጥፎ” ነገር እንደሚቆጠር አላውቅም ነበር፡፡ ለዛ ይመስለኛል፡፡

ቤን፡  ስለአስተዳደግህ ካነሳህልኝ ዘንዳ … እስቲ አጫውተኝ

ቪክ፡  ያደግሁት በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ….

ቤን፡  ሃሃሃሃሃሃ…. እስቲ አትቀልድ… በስርዓት አዋራኝ

ቪክ፡  እንዴ… የምሬን እኮ ነው! አዲስ አበባ ነው ተወልጄ ያደግሁት፤ እና እንደነገርኩህ … ከቤት ሳልወጣ … ከሰኞ እስከ አርብ ትምህርት ቤት … ከዛ ቅዳሜ እና እሁድ ከቤት መውጣት የለም፤ እሁድ ማታ ለሰኞ ልብሳችንን እና ደብተራችንን አዘጋጅተን ማደር አለብን … ቤቴሴባችን በጣም ጥብቅ ነበር ፤ ፋዘር እንደ ወታደር ፕሮቶኮሉ ጥብቅ ነበር ፣ እናቴ ደግሞ በመጠኑም ቢሆን ከሱ ፈታ ያለች ነበረች፡፡ እንደ አሁን ከባድ ባይሆንም ያኔም ኃይማኖተኛ ነበሩ፤ … ከጎረቤት ልጅ ጋር እንኳን እየተጫወትኩ አላደኩም፡፡ ግቢያችን ውስጥ ነበር እድገቴ፡፡

ቤን፡  ለዛ ነው ራስህን ለሰው እንዲስማማ ብለህ ስታርም የማናይህ

ቪክ፡  ይመስለኛል፡፡ አባቴ ብቻ … ጓዳ ገባህ … የሴት ስራ ሰራህ .. ምናምን ይለኝ ነበር እንጂ … የማህበረሰቡ አኗኗር እንዲህ ነው … እንዲህ መሆን አለብህ … እንዲህ አታድርግ እየተባልኩ አላደኩም፡፡ የአባቴንም እንደ ጨዋታ እና ቀልድ ነበር የማየው፡፡ ከኛ ቤት ውጪ ያለውን አኗኗር ስለማላውቀው ይሄኛው ትክክል ፣ ያኛው ስህተት ነው የሚል ግንዛቤ አልነበረኝም ፤ የለብኝምም፡፡

የተማርኩትም በጣም ወጬጌ የሆነ ትምህርት ቤት ነው፡፡ ስሙን አልጠቅሰውም.. ሃሃ፡፡ ጠዋት ጠዋት ራሱ ባንዲራ የሚሰቀለው በዜግነት ክብር አይደለም … በመዝሙር ነበር፡፡ ግብረ ገብ እንማር ነበር … ከዛ ዓርብ ዓርብ ጠዋት ቤተክርስቲያን እንሄዳለን፡፡ … ቤትም ፣ ትምህርት ቤትም ኃይማኖተኛ ሆነው ነው ያደግሁት፡፡

ቤን፡  እንዴት ነበር ታዲያ የዜግነት ትግሉ?

ቪክ፡  ሃሃሃ … በዕውነቱ… ትግሉ አስቸጋሪ ነበር፡፡

ቤን፡  ፖለቲካ አስመሰልነው

ቪክ፡  እኮ… የሚያስቀው ደግሞ … ቤት ፕሮቴስታንት ነበርን ፣ የምማርበት ትምህርት ቤት ደግሞ የኦርቶዶክስ ነበር፡፡ እና በሁለት በኩል ነበር ኃጥያት እንደሆነ ነበር ስንማር ያደግነው፡፡ የኔን ስሜት የሚመስል ነገር የማይበት አጋጣሚው አልነበረኝም፡፡

ቤን፡  ጥሩ… ለነገሩ ብዙዎቻችን በተመሳሳይ ዓይነት አስተዳደግ ውስጥ ያለፍን ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን አሁን ላለን ማንነት መሠረት የራሱ የሆነ ትልቅ አስተዋፅዖ አለውና … አቀባበላችን እንዴት ነበር? መቼስ ራሳችንን ለማግኘት ወሰንን? የሚለውን ነገር የምንወስንበት የህይወታችን ቦታ ይወስነናል ብዬ አምናለሁ፡፡ መቼ ነበር ያንተ “አሃ” ያልክበት አጋጣሚ? ስለ ፆታዊ ተማርኮህ ያወቅኸው ፣ አውቀህስ ስለዚህ ነገር የበለጠ መረዳት እንዲኖርህ የወሰንከው መቼ ነበር?

እንዳልከኝም … ቤተሰቦችህ ኃይማኖተኞች ናቸው፤ ያም ማለት በእርግጠኝነት አንተም በቤተክርስቲያን ትምህርት ውስጥ እንዳለፍክ አያጠራጥርም…

ቪክ፡  ኧረ መሪ ሁሉ ነበርኩ! ሃሃ

ቤን፡  ሃሃ… አዎ! … እና እስቲ ስለሱ አጫውተኝ፤ ስለ ሙግትህ፤ ከማህበረሰቡ ጋር ሳይሆን ከራስህ ጋር ስለነበረህ ሙግት ፤ እንዴትስ አልፈኸው አሁን ያለህበት የህይወት ሁኔታ ላይ ደረስክ?

ቪክ፡  ቀላል አልነበረም፡፡ በትንሽ ጊዜ የተፈታም ነገር አልነበረም፡፡ እንዳልኩህ ከቤት ሳልወጣ ነው ያደግሁት … እና ስለ ማንኛውም ፆታዊ ተማርኮ ምንም የማውቀው ነገር አልነበረም፡፡ ለምሳሌ… 13 ዓመቴ ላይ የመጀመሪያ ህልመ ሌሊት ሲያጋጥመኝ … ሃሃሃ… ወንድ ነበር በህልሜ ያየሁት፡፡ ምን እንደወጣኝ ራሱ አላውቅም ነበር ፤ ቤትም ሆነ ትምህርት ቤት ማንም ስለ ህልመ ሌሊት የነገረኝ የለም ነበር፡፡ እና … ያኔ ወንድ ሳይ  … ሰይጣን በህልሜ ተገልጦ የሆነ ነገር ያደረገኝ ነበር የመሰለኝ፡፡ ሃሃሃሃ … በጣም ነበር የሚከብደው፡፡

ትምህርት ቤትም እኔ ክፍል የነበሩ ልጆች … ያው ጉርምስና ላይ ስለነበርን … ስለ ሴት ፣ ስለ ጡት ምናምን ሲያወሩ እኔ ምንም አይገባኝም ነበር፡፡ እና ያስጠላ ነበር፡፡

የነበረኝ አማራጭ ቤተክርስቲያን ማዘውተር ነበር፡፡ ቤተክርስቲያን የማልሄደው ሰኞ እና ሀሙስ ብቻ ነበሩ፡፡ ብዙ ነገሮች ላይ እሳተፍ ነበር፡፡ የትምህርት ቤት መፅሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲሁም ፌሎውሺፕ ዋና አስጠኚ ነበርኩ… ቸርች የሆነ ነገር መሪ ነበርኩ… ብቻ ሁሉም ውስጥ ነበርኩበት፡፡ ጌታ ያንን ትጋቴን አይቶ ይፈውሰኛል የሚል ዕምነት ነበረኝ፡፡ ጊዜዬን በሙሉ ቤተክርስቲያን ላይ ማሳለፌ ይሔን ነገር እንዳላሰላስለው ፣ ብሎም እስከመጨረሻው እንዲጠፋልኝ ይረዳኛል ብዬ፡፡

ቤን፡  ሃሃሃሃ … የኦርቶዶክስ ትምህርት ቤት እየተማርክ ግን  የፕሮቴስታንት ፌሎውሺፕ መምራት አይከብድም?

ቪክ፡  ተደብቀን ነዋ! በሚስጥር ነበር የምንሰባሰበው፡፡ የኦርቶዶክስ ትምህርት ቤት ቢሆንም የተለያየ ኃይማኖት ያላቸው ተማሪዎች ነበር የሚማሩበት፡፡

ቤን፡  እና ድብብቆሹን ያኔ ነው የጀመርኩት እያልከኝ ነው

ቪክ፡  ሃሃሃ … እሱ ነው ያለማመደኝ፣ ተደብቆ መኖሩን፡፡ ያኔ ደግሞ… ጴንጤ ጴንጤ እየተባልን የምንገለልበት ጊዜ ነበር፡፡ ሽማግሌ ያስመስለኛል … ግን እንደዛ ነበር፡፡

ቤን፡  እና … በዚህ ሁሉ ውስጥ አልፈህ … ማለቴ… መፅሐፍ ቅዱስ ስለማንነትህ ምን እንደሚል ታውቃለህ፤ እንዴት ታረቅከው? እንዴት ከራስህ ጋር አስማማኸው?

ቪክ፡  መፅሐፍ ቅዱስ ሳነብ ፣ ወይም ደግሞ ቸርች ውስጥ ስብከት ስሰማ ምናምን … ስለ “ግብረሰዶማዊነት” ሲሰበክ … “ሰማሽ? ላንቺ ነው የሚወራው” እላት ነበር ውስጤን፡፡ ሃሃሃ

እኔንጃ …. በጣም ይጨንቀኝ ነበር፡፡ አንድ ጊዜ እንዲያውም ፀሎት ላይ … የሴት መንፈስ አድራበት ሌሊት ሌሊት ትመጣበታለች… ምናምን ሲባል … እኔ ነኝ ጌታ ሆይ ብዬ እዬዬ ስል አስታውሳለሁ፡፡ አሁን ሳስበው እኮ … እኔ አልነበርኩም፡፡ ብቻ… የምትባለው ነገርን ውስጥህ ካለው ነገር ጋር ለማስማማት በጣም አስቸጋሪ ነበር፡፡

ቤን፡  ከባድ ነው፡፡ እንኳን እንዲህ ከአብዛኛው ሰው የተለየ እና “የተወገዘ” ፆታዊ ተማርኮ ኖሮን ፣ አንድ አይነት ተማርኮ እንኳን ቢኖረን … የእያንዳንዳችን ውስጣዊ ማንነት የተለያየ ይመስለኛል፡፡ የየራሳችን ዕውነት ፣ የየራሳችን ለህይወት ያለን አመለካከት  ምናምን በጣም የተለያየ ነው፤ እና ያንን ነገር የመረዳቱ ሁኔታ ላይ ይመስለኛል የሚቀጥለውን የህይወታችንን ምዕራፍ ገፅታ የሚቀርፅልን፡፡

እና እንዴት አለፍከው ታዲያ? ምን አጋጠመህ?

ቪክ፡  ተስፋ ቆረጥኩ ልበል? … እንደዛ ካልኩ ደግሞ ኃይማኖታዊ ተከራካሪዎች ተስፋ ስለቆረጥክ ነው እንዲህ የሆንከው ሊሉኝ ነው፡፡ በቃ … ራሴን ብቻ … ከውጪ የምሰማውን ምናምን ትቼ ውስጤን ማዳመጥ ጀመርኩኝ፡፡ 

ቤን፡  ይቅርታ አድርግልኝ እና … ተስፋ ብትቆርጥም እኮ ለራስህ ትክክል ነህ ፤ የራስህ ስሜት ነው፡፡ ራስህን የምታውቀው አንተ ነህ፡፡

ቪክ፡  አዎ! ግን … ኃይማኖተኛ ተከራካሪዎች እንደዛ ስትላቸው … ዕምነት ስለሌለህ ፣ ተስፋ ስላጣህ ነው ጌታ አሳልፎ የሰጠህ ይሉሃል፡፡  እኔ እኮ እረዳዋለሁ … ግን ያው የቋንቋውን ፖለቲካ ታውቀዋለህ፡፡ ለነሱ መንገድ ላለመስጠት ነው፡፡ እና ተስፋ ቆረጥኩ ስል … የራሴ ማንነት የማይቀየር እንደሆነ ተረዳሁ ለማለት ነው፡፡

የቤተክርስቲያን ተሳትፎዬን ሳቋርጥ … በአንድ ቀን ነው ርግፍ አድርጌ የቀረሁት፡፡ የዛሬ 10 ዓመት አካባቢ ነው መሰለኝ … ካስታወስክ የሆነ ቪሲዲ ወጥቶ ነበር፡፡  የግብረሰዶማውያን ምናምን የሚል ፣ በጣም የተሳሳቱ ነገሮችን የያዘ ሲዲ ነበር፡፡ ከእንስሳ ጋር ሴክስ ያደርጋሉ … እንዲህ ናቸው ፣ እንዲያ ያደርጋሉ ፣ እንደገና ደግሞ አንዳንድ ወጣ ያሉ የወሲብ ቪዲዮዎች ተቀንጭበው የተካተቱበት ሲዲ ነበር፡፡ እንግዲህ ይታይህ … በዛ ሲዲ ቤተክርስቲያን ውስጥ እያሳዩ ያስተምሩበት ነበር፡፡ እና የወጣ ሰሞን አንድ ቀን እኔ አልሄደኩም ነበር ፤ እናቴ ከቤተክርስቲያን ስትመለስ ያንን ተምራ ሲዲውን ይዛ መጥታ ላንተ ይሆናል ብላ ሰጠችኝ፡፡

ቤን፡  እንዴ! ለምን ላንተ?

ቪክ፡  ምን አውቅላታለሁ! ሃሃሃሃ …. ሁለት ነበር ይዛ የመጣችው ፤ አንዱን ለእኔ ፣ አንዱን ደግሞ ቢሮ ሌላ ልጅ አለ.. ለሱ መስጠት እፈልጋለሁ አለችኝ፡፡ ደግነቱ ሲዲው በሆነ ምክንያት አይሰራም ነበር፡፡ እሷ ግን እዛም ተምራው ስለነበር ይዘቱ ምን እንደሆነ ስታብራራልኝ … በቃ፤ ከዛ በኋላ ቤተክርስቲያን መሄዴን አቆምኩ፡፡ ለሰርግ ብቻ ነው የምሄደው … እሱንም ኮክቴል ካለው፡፡ ሃሃሃ

እና ቀረሁ ቀረሁ፡፡ በእግዚአብሔር ተስፋ ቆርጬ ምናምን አይደለም፤ ነገር ግን እዛ ያሉት ሰዎች ከጥላቻ የተሻለ ነገር ሊያሳዩኝ ስላልቻሉ … በቃኝ፡፡ የሚያሳዝነው ግን … ጠፋህም ብሎ የፈለገኝ የለም፡፡ ሃሃሃ

ቤን፡  ዴት እያደረግክ ነው?

ቪክ፡   (ረጅም ፀጥታ) ሃሃሃሃ …. አይደለም!

ቤን፡  ምነው አመነታህ! … ፈላጊ አግኝቼልህም ሊሆን ይችላል እኮ!

ቪክ፡  ይኼን አንብበው ያናግሩኛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ! … ኢንቦክስ አድርጉልኝ እናንተ!

ቤን፡  ሃሃሃ…. እሺ .. እስቲ አሁን ደግሞ ስለ እኛ … ስለ ዜጋውና ስለ አጠቃላይ ማህበረሰቡ … በመሃላችን ስላለው ግንኙነት … ብዙ ጊዜ ጥላቻ ላይ የተመረኮዘ ቢሆንም ምን አይነት እይታ አለህ? የፆታዊ ተማርኮ ግንዛቤን ለመፍጠርስ ምን ዓይነት መንገዶችን መጠቀም አለብን ትላለህ?

ቪክ፡  እንደሚታወቀው አብዛኛው ህብረተሰብ መጥፎ አመለካከት ነው ያለው፡፡ ያ የጥላቻ አመለካከት ደግሞ ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል ኃይማኖትን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ከዛም ባለፈ ፆታዊ ተማርኮ … ምንድን ነው ብለህ ብትጠይቅ አብዛኛው ሰው የሚመልስልህ … ከሰዶም እና ገሞራ መጥፋት ጋር አያይዞ ነው፡፡ ከዛም ገፋ ቢል ደግሞ … ሰው ይደፍራሉ ፣ ይመለምላሉ ፣ 666 ምናምን እያሉ ሰው ያወራላቸውን ነገር ይደግሙልሃል እንጂ ጠለቅ ባለ መልኩ መርምረው ለማወቅ የሚነሳሱ አይደሉም፡፡ እና ከትልቅ የግንዛቤ ክፍተት የመጣ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ እኔ አሁን በግሌ አንድ ሰው እፀልይልሃለሁ ምናምን ቢለኝ አይደብረኝም ፤ ማንነቴን ተመርኩዞ ሰብዓዊ መብቴን አይንፈገኝ … ነፃነቴን አይግፈፈኝ እንጂ …. መፀለይ ይችላል፡፡

እና ምናልባት … በተለይም ሶሻል ሚዲያ ላይ ዜጋው … አሁን ካለንበት የተከለለ የሶሻል ሚዲያ ድንበር ወጣ ብሎ … ሁሉንም አሳታፊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ቢሳተፍ ፣ ስለ ዜጋ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ሀገራዊ ፣ ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚነሱ ውይይቶች ላይ ቢካፈል ፣ ባለን የዜጋ አካውንትም ቢሆን አድማሳችንን ሰፋ አድርገን … ደህንነታችንን በጠበቀ መልኩ … ልክ እንደማንኛውም ሰው ቁምነገራዊ የሆኑ ጉዳዮች ላይ ዕውቀቱም ፣ ልምዱም ፣ ፍላጎቱም እንዳለን በማሳየት ግንዛቤን ማስጨበት የምንችል ይመስለኛል፡፡ ቢያንስ የሉም የሚለውን አስተሳሰብ አፍርሶ … እንደ አውሬ የሚያዩንን … ሰው መሆናችንን ማሳየት እንችላለን ብዬ አስባለሁ ፤ በእኛ ሀገር ነባራዊ ሁኔታ ሳየው፡፡

እና ጥላቻቸው ከምን የመጣ ፣ ከየት ያገኙት እንደሆነ ስለምረዳ ያን ያህል አያስጨንቀኝም፤ ይገባኛል፡፡ ራሳችንንስ ጠልተን እናውቅ የለ? … እኔ እንኳን ወደ ሃያ አመት አካባቢ ከፈጀብኝ … ራሴን ለማወቅ እና ለማክበር ፣ ያልሆነው ደግሞ የማያውቀውን ዕውነት ለመቀበል ምን ያህል ጊዜ እንደሚፈጅበት መረዳት ቀላል ነው፡፡ ያ ይመስለኛል ቀለል ያረገልኝ፡፡

ቤን፡  በጣም አሪፍ፡፡

ቤን፡  የተከፋህበት ጊዜ አለ? ዜጋ በመሆንህ የተቆጨህበት… ወይም ባልሆንኩ ብለህ የተመኘህበት ጊዜ? የደረሰብህ መገለል ወይም ጥቃት ….

ቪክ፡  የደረሰብኝ ነገር ሳይኖር ቀርቶ አይደለም ፡ ግን እንደዛ አስቤ የማውቅ አይመስለኝም – አላውቅም፡፡ ማንነቴን አውቄ .. አምኜ ከመቀበሌ በፊት “ለመፈወስ” የምሞክርበትን ጊዜ… ዜጋ ነኝ ብዬ ገና አላመንኩም ነበርና አልቆጥረውም፡፡ ራሴን ከተቀበልኩ በኋላ ግን በስድብ እና በጥላቻ ምክንያት ምነው ባልሆንኩ ብዬ አማርሬ አላውቅም፡፡

ቤን፡  እንዴት? ይህን ጥንካሬህን ከምን አገኘኸው?

ቪክ፡  ጥፋቴ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ምናልባት ለምን እዚህ ሀገር ተፈጠርኩ ብዬ አስቤ ይሆናል እንጂ … ለምን እንዲህ ሆኜ ተፈጠርኩ ብዬ አላውቅም፡፡ መጥፎ ነገር ነው ብዬ ስለማላስብ ነው፡፡ በዜግነቴ አፍሬም ሆነ ተሳቅቄ አላውቅም …. ምናልባት ያለሁበትን ነባራዊ ሁኔታ ፣ ህብረተሰቡን … ለምን እንደዚህ ሆኑ እል ይሆናል፤ ሃሃ… ምነው ጌታ ሆይ እንዲህ አደረካቸው ብዬ ፀልዬ አውቃለሁ! ሃሃሃሃሃሃ

(ይቀጥላል)