ጥያቄ፡ በመጀመሪያ የቡና ግብዣዬን ስለተቀበልከኝ እና ልታወራኝ ስለፈቀድክ ፣ እንዲሁም የመጀመሪያ እንግዳዬ በመሆን መሞከሪያዬ በመሆንህ …. እጅግ ላመሰግንህ እወዳለሁ፡፡
ናቲ፡ ሃሃ…. እኔም ስለጋበዝከኝ አመሰግናለሁ፡፡
ጥያቄ፡ እንዴት ነበር የጀመርከው?
ናቲ፡ ምን…ዜግነት? ሃሃ
ጥያቄ፡ እ? እንዴት ነበር የመጀመሪያ ጊዜህ?
ናቲ፡ የመጀመሪያ ጊዜ ሰው ያገኘሁት ከ12 ዓመት በፊት ነበር፡፡ ግቢ ነበርኩ፡፡ ከዛ ረፍት ላይ ከሀገር ውጭ የመሄድ አጋጣሚ ገጥሞኝ ነበር፡፡ እዛ ነው የመጀመሪያ ሀበሻ ዜጋ ያገኘሁት፡፡
ጥያቄ፡ እንጂ …. ተደፍረህ ወይም ነጮች አስተምረውህ አይደለም?
ናቲ፡ ሃሃ… እስቲ አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ? እኔ ይኼ ደፈራ ምናምን የሚባለው ነገር አይገባኝም፡፡ በቀላሉ ለማስረዳት …. ተገደህ የተደረግከውን ወይም የተደረገብህን ነገር ትጠላዋለህ እንጂ… መልሰህ አንተ አታደርገውም እኮ…. አይደል እንዴ? እንዲያውም ከዕድገታችን ፣ ከማህበረሰባችን ፣ ከሌሎች ሰዎች የሚመጣውን ጥላቻ ለመቋቋም እና እኛም በዛ ጥላቻ ውስጥ አድገን ራሳችንን እንድንጠላ ስለተደረግን…. ለራሳችን ጥሩ ስሜት እንዲሰማን ፣ ከራሳችን ማምለጫ መንገድ ወይም አባባል ይመስለኛል፡፡
ጥያቄ፡ ልክ ነው፡፡ ከ12 ዓመት በፊት እንዴት ነበር?
ናቲ፡ እንደ አብዛኛው ሰው ነበር፡፡ ልጅ ሆኜ የተለየሁ መሆኔን አውቅ ነበር፡፡ ያን ያህል የተቸገርኩበት ነገር አልነበረም፡፡ ዜጋ መሆኔን እንደተረዳሁ ተቀብዬዋለሁ፡፡ ነገር ግን ከእኔ ሌላ ሰው የለም ብዬ አስብ ስለነበር እንደማንኛውም አካባቢዬ እንደነበሩት እኩዮቼ የሴት ጓደኛ ያዝኩኝ፡፡ ከዛ ከሀገር ውጪ ያልኩህ አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡
ጥያቄ፡ የሴት ጓደኛ ነበረህ (ሃሃሃሃሃ)
ናቲ፡ ምናባህ? ምን ያንሰኛል? ሃሃሃሃሃ
ናቲ፡ ያው እንዳልኩህ… ሰው የሚሆነውን ነበር የምንሆነው፡፡ ስሜቱ ቢኖረንም ዕውቀቱ ብዙም አልነበረንም፡፡
ጥያቄ፡ እና እዛ ያገኘኸውን ሰው ዜጋ መሆኑን እንዴት አወቅህ?
ናቲ፡ አንድ ሆቴል ውስጥ ነበርን፡፡ እሱም ብቻውን ነበር መሰል፡፡ በቃ ድንገት ተዋወቅን – አማርኛ ስናወራ ሁለታችንም መስማታችን ይመስለኛል፡፡ ከዛ ማውራት ጀመርን ፡ ሀገሩን ልናይ አብረን ወጥተን ነበር ምናምን፡፡ ከዛ ልመለስ ሦስት ቀን ሲቀረኝ “ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ እንዲህ ዓይነት ሰው እንዳለ ታውቃለህ ወይ?” ብሎ ራሱ ጠየቀኝ፡፡
ጥያቄ፡ “አዎ እኔ አለሁ!” አልክ? ሃሃሃ
ናቲ፡ ሃሃሃሃሃሃ ….
ጥያቄ፡ በዛን ሰዓት ግን.. እንዴት ነበር ስሜቱ? ያን ጥያቄ ሲጠይቅህ ምን ተሰማህ?
ናቲ፡ ሁለታችንም ሳናውቀው የተዋወቅን ይመስለኛም መጀመሪያዉኑ፡ ሃሃሃ አንድ ሳምንት ሙሉ እንተያይ ነበር ፣ እናወራ ነበር… ከሴት ጋር አላየውም ፣ ከሴት ጋር አያየኝም … ምሳ ሲበላ “ ናቲ … ና ምሳ እንብላ!” እያለ ይዞኝ ነበር የሚወጣው .. እኔም ስፈልገው አለ…. አውጥተን አላወራነውም እንጂ … ሁለታችንም የተግባባን ይመስለኛል፡፡ ከዛ አወራን….
ጥያቄ፡ በቃ? በወሬ ብቻ ተለያያችሁ? ሃሃ
ናቲ፡ ሃሃሃሃ…. እና ሌላ ምን ፈለክ?
ጥያቄ፡ አይ… ከተግባባችሁ… አለ አይደል? ሃሃሃሃ
ናቲ፡ የሆንክ! እና ምን ጠብቀህ ነበር? ግን… ክለብ ሄደን ነበር፡፡ የዜጋ ክለብ፡፡
ጥያቄ፡ የመጀመሪያ ጊዜ ሰው አግኝተህ … የመጀመሪያ ጊዜ የዜጋ ክለብ ገብተህ….?
ናቲ፡ ሃሃሃሃ…. ሁሉንም ባንዴ! ለነገሩ … ክለብ ክለብ አልነበረም፡፡ ባር ነገር ነበር፡፡
ጥያቄ፡ አልደነገጥክም?
ናቲ፡ ምን የሚያስደነግጥ ነገር አለ? ያው ሰው ነው የነበረው፡፡
ጥያቄ፡ ከዛስ?
ናቲ፡ ከዛ በቃ…. ሌላ ፌስቡክ አካውንት ከፈትኩ፡፡ የብዙዎቻችን ተመሳሳይ ታሪክ ነው፡፡ ፌስቡክ ላይ ሰው መፈለግ ጀመርኩ … አንዳነድ ሰዎችን ማውራት ጀመርኩ… ከዛ በቃ…. ጓደኞቼን ተዋወኩ፡፡
ጥያቄ፡ ብዙ ጊዜ … ራስን በመፈለግ ሂደት ውስጥ ይኼን የኛን የዜጋውን ሕብረተሰብ ስትተዋወቅ የሚያገጥምህ የመጀመሪያው ሰው ወይም ግሩፕ ከዛ በኋላ ያለህን አመለካከት በመቅረፁ በኩል ትልቅ አስተዋፅዖ እንዳለው በተለያዩ አጋጣሚዎች ፣ በራሳችንም ልምዶች የምናየው ነው፡፡ እንዴት ነበር ያንተ ልምድ?
ናቲ፡ ዕድለኛ ነበርኩ ማለት እችላለሁ፡፡ በዛን ጊዜ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተዋወኳቸው ጓደኞቼ ጋር አሁንም ጓደኛሞች ነን፡፡
ጥያቄ፡ አዎ፡፡ ለምሳሌ…. እኔም በመጀመሪያዎቹ ራሴን እና ኮሚኒቲዬን በምተዋወቅበት ጊዜያት ያገኘኋቸው ጓደኞቼ አሁን ላለኝ ማንነት እና አመለካከት አስተዋፅዖ አበርክተዋል፡፡ አካባቢዬ የነበራችሁት በሙሉ ያሳያችሁኝ ፍቅር እና ድጋፍ ለዜጋው ማህበረሰብ መልካም የሆነ አመለካከት እንዲኖረኝ እና ፣ ብሎም ራሴን የመቀበሉን ፣ ከራሴ ጋር የመታረቁን ሂደት በእጅጉ እንዲቀልልኝ አድርጎኛል፡፡
ናቲ፡ ሃሃሃ… ይገባናል ይገባናል!
ናቲ፡ ልክ ነህ፡፡ ጥሩ ጓደኛሞች ነን፡፡
ጥያቄ፡ እሺ …. ፌስቡክ ላይ ፣ አልፎ አልፎም በአካል ፣ የዜጋውን ማህበረሰብ ጤና ለመጠበቅ የሚረዱ መረጃዎችን እና ትምህርቶችን በማሰራጨት ከሚንቀሳቀሱ ሰዎች አንዱ ናቲ ፍቅር ነው፡፡ እንዲያውም ከመጀመሪያዎቹ መሀል እንደምትመደብ እኔ በግሌ አምናለሁ፡፡ እንዴት ወደዚህ እንቅስቃሴ መጣህ?
ናቲ፡ ልክ ነው፡፡ እኔ ዜጋውን ህብረተሰብ የተዋወቅሁበት ወቅት አካባቢ የተለያዩ ዝግጅቶችን የሚያዘጋጁ ፣ ስለ ጤናማ ወሲብ የሚያውቁትን መረጃዎች የሚያካፍሉ…. ያው የሀገራችንን ሁኔታ ታውቀዋለህ … በድብቅ ስለምንኖር እና ፣ የተገለልን ስለሆንን እኛን ያማከለ የጤና ፕሮግራም ወይም ትምህርት ስለሌለ… ያንን ቀዳዳ ለመሸፈን የሚንቀሳቀሱ ታላላቆቻችን ነበሩ፡፡ ላባ ግሩፕ ይባሉ ነበር፡፡ አባላቶቹ አሁንም አሉ፡፡ በኋላ ላይ ግን ይህ እንቅስቃሴ እየተዳከመ ሲመጣ ፣ ከነሱ መሀል አንዱን ልጅ አውቀው ስለነበር ፣ ከሱ ጋር አንዳንድ ነገሮችን በማድረግ ነበር የጀመርኩት፡፡ በዚህ አጋጣሚ ላመሰግነው እወዳለሁ … ከዛ ሳላውቀው በጊዜ ሂደት ስራው ውስጥ ገባሁ፡፡
ጥያቄ፡ በዚህ አጋጣሚ …. እኔም አሁን ድረስ አንተና ጓደኞችህ ለህብረተሰባችን መልካም ሕይወት የምትሰሩትን መልካም ስራ በቅርበት አውቃለሁና ላመሰግናችሁ እወዳለሁ፡፡
ጥያቄ፡ ከዛስ እንዴት ሆነ?
ናቲ፡ ከዛ … አብዛኞቹ አባላት በተለያየ ምክንያት ከሀገር ሲወጡ ፣ እዚህም ሆነው ሲርቁ …. አብዛኛውን ነገር እኔ ነበርኩ ተረክቤ የቀጠልኩት፡፡ ሉብሪካንት የሚያመጡልንን ሰዎች ተዋወቅሁ … ከዛ ከጓደኞቼ ጋር ሆነን ሰዎች እያገኘን ማከፋፈል ጀመርን፡፡
ጥያቄ፡ የሉብሪካንት ጅምላ አከፋፋይ ሆኜ ቀረሁ እያልክ ነው! ሃሃሃ
ናቲ፡ ሃሃሃ…. ምን ታደርገዋለህ እንግዲህ፡፡
ጥያቄ፡ ዱሮ ዱሮ የላባ አባላት የሚያዘጋጇቸው ዝግጅቶች ከመጀመራቸው በፊት ፣ ወይም መሀል ላይ ሰዎች ጤናቸውን እንዲጠብቁ መልዕክቶች ይተላለፉ እንደነበር ፣ ኮንዶም እና ሉብሪካንትም ይከፋፈል እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡ እውነት ነው?
ናቲ፡ አዎ! የእነዚህ ዝግጅቶች ዋነኛ አለማ ዜጋው ጤናውን እየጠበቀ እየዲዝናና ነበር፡፡ ፓርቲ ብቻ አልነበረም፡፡ ሰዎች ቀደም ብለው ተገናኝተው አብረው ራት ይበላሉ ፣ ይወያያሉ ፣ ይደጋገፋሉ፡፡
ጥያቄ፡ ቅድም የላባ ግሩፕ እንቅስቃሴ እየተዳከመ መምጣቱን ጠቅሰህልኝ ነበር፡፡ ምንድን ነበር ምክንያቱ?
ናቲ፡ ያው ያኔ እንደዛ ያሉ ተሰብስበን የምንማማርባቸው ፣ የምንደሰትባቸው ፣ የምንተዋወቅባቸው ዝግጅቶች ለዜጋው ማህበረሰብ አዲስ ነገር ነበሩ፡፡ እናም እንዴት ልንጠቀምባቸው እንደሚገባ በደንብ ያወቅን አይመስለኝም – በዛን ጊዜ፡፡ ጠብ እና ድብድብ በሽ ነበር፡፡ ሰዎች አካላዊ ጉዳት እስኪደርስባቸው ድረስ፡፡ ያ ይመስለኛል ላባዎችንም እንዲቀዛቀዙ ያደረጋቸው፡፡
ጥያቄ፡ እስቲ አሁን ወዳለንበት/ወዳለህበት እንምጣ፡፡ አዲስ አሊያንስ ምንድን ነው?
ናቲ፡ አዲስ አሊያንስ በአጭሩ የዜጋውን ማህበረሰብ አካላዊ እና አዕምሮአዊ ጤና ለመጠበቅ የሚረዱ መረጃዎን በማሰራጨት ፣ እንዲሁም በሌሎች የጤና ማዕከላት በሴክሹዋሊቲያችን ምክንያት ማግኘት የማንችላቸውን አገልግሎቶች በተቻለ መጠን ለማሟላት የሚንቀሳቀስ ቡድን ነው፡፡
ጥያቄ፡ እንቅስቃሴውን በቅርበት አውቀዋለሁና … ስለምትሰሩት ስራ ሳላመሰግናችሁ አላልፍም፡፡ ከእናንተ በተጨማሪም በተመሳሳይ ሁኔታ 1ዜጋ አለ፡፡ እንዴት ነው… ሁለቱ ቡድኖች ብቻ ያሉብንን ችግሮች ሙሉ በሙሉ ፈትተዋል ባይባልም በጤናው ዘርፍ የማይናቅ አስተዋፅዖ እያደረጉ ነው፡፡ ነገር ግን የተሻለ ውጤት ለማግኘት…. በተለይም አሁን ላይ እኛ በስንት ትግል … ስንት ዘመን ፈጅቶብን ያወቅናቸውን ነገሮች … የተማርናቸውን ትምህርቶች እና ልምዶች በቀላሉ ቀድመው አውቀው እና በጣም ብዙ የሆነውን የሴክሹዋሊቲ ስፔክትረም የሚወክሉ ወጣቶች እየበዙ ባለበት ሰዓት…. ከሁሉም አይነት የህብረተሰባችን ክፍል የሚወከሉ እንቅስቃሴዎች ቢኖሩ… የተሸለ ይሆናል የሚል አስተያየት አለኝ፡፡ ምን ትላለህ፡፡
ናቲ፡ ልክ ነው፡፡ ያስፈልገናል፡፡ እኔ ራሱ አልፎ አልፎ ወጥቼ ሰዎችን በማገኝበት ሰዓት የማላውቃቸው ብዙ ወጣቶችን አያለሁ፡፡ ነፃነታቸው ደስ ይላል…. ያንን ነፃነታቸውን የሚጠብቅ እና የሚፈልጉትን ህይወት እንዲመሩ የሚያበረታታ ነገር ያስፈልጋቸዋል፡፡
ጥያቄ፡ እስቲ የምትጧቸውን አገልግሎቶች አንዳንዶቹን ጥቀስልን
ናቲ፡ በዋናነት ያው የስነ ተዋልዶ ጤና መረጃዎችን በፌስቡክ ፔጃችን እና በዌብሳይታችን እናቀብላለን፡፡ በተጨማሪ ደግሞ አሁን አዲስ የቴሌግራም ቻናል ከፍተናል፡፡ ከሁሉም ከሁሉም ግን “አዲስ ጤና” የሚል የሞባይል አፕሊኬሽን ለቀናል… ብዙ መረጃዎችን የያዘ አፕሊኬሽን ነው፡፡
ከዛ በተረፈ … ሰዎች ኤች አይ ቪ እና ሌሎች የአባላዘር በሽታዎች ላይ ትኩረት አድርገው ፣ ተመርምረው ጤናቸውን አውቀው … ህይወታቸውን በጤንነት እንዲመሩ እናበረታታለን ፣ ወቅታዊ የሆነ የምርመራ ዘመቻም እናካሂዳለን፡፡
ጥያቄ፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ… ታስታውስ እንደሆን… ያኔ… የዜጋው እንቅስቃሴ ወደ ፌስቡክ የመጣበት ጊዜ አካባቢ ብዙ ሰው ፌስቡክን ልክ እንደ አሁኑ ግራይንደር ለሴክስ መገናኛ ነበር የሚጠቀምበት፡፡ ብዙ ወሲባዊ ፕሮፋይል ፒክቸሮችንም ማየት የተለመደ ነበር፡፡ አሁን አሁን ላይ ግን ፌስቡክ እንደ ማህበራዊ ትስስር መድረክነቱ … ብዙ ሃሳቦች የሚንሸራሸሩበት ፣ ጓደኝነት የሚመሰረትበት ፣ ሰዎች የሚማማሩበት መድረክ ሆኗል፡፡ ለዚህም ለውጥ አንተን ጨምሮ እዚሁ የምናውቃቸው ጓደኞችህ ፌስቡክ ላይ የጀመሩት እንቅስቃሴ የማይናቅ አስተዋፅዖ እንዳለው አምናለሁ፡፡
ናቲ፡ ልክ ነህ ብል ማጋነን አይሆንብኝም፡፡ በተለይም የምንተዋወቀው የተወሰንን ሰዎች ያንን የተለመደ “ለሴክስ እንገናኝ” ልምድ ትተን የተለያዩ ጉዳዮች ላይ መወያየት መጀመራችን ፣ እርስ በርስ መቀላለዳችን …. በተለይም ደግሞ ስለራሳችን ፣ ስለዜግነታችን ጉዳዮች እንድነወያይ ፣ እንድንማማር … የ ዜጋ ማተርስ ፔጅ መከፈት ፣ የተለያዩ መረጃዎችን ሼር የምናደርግበት “የኢትዮጵያ ዜጋ ላይብረሪ” የሚባለው ሌላ ፔጅ መፈጠር… እንዲሁም ሌሎች የመፃፍ ፣ የመቀለድ ችሎታ ያላቸው ልጆች የሚያጋሩን ታሪኮች እና ልምዶች አትሞስፌሩን ቀይሮታል ብዬ አምናለሁ፡፡ ይኼ የፌስቡክ የአንድነት መንፈስም ነው የ1ዜጋ እና የአዲስ አሊያንስ ምስረታ መሠረት፡፡
ጥያቄ፡ ምናልባት ናቲን የሚከጅሉ ካሉ ቅስማቸውን ልስበረውና… ረዘም ላለ ጊዜ በሪሌሽንሺፕ ላይ እንዳለህ አውቃለሁ፡፡ ምን ያህል ጊዜ ሆናችሁ ከጓደኛህ ጋር?
ናቲ፡ ሃሃሃሃ…. ብዙ ሆኖ አይደለም… ግን 4 ዓመት ሆኖናል፡፡
ጥያቄ፡ እንዴ…. ብዙ አይደለም? ለአንዳንዶቻችን እኮ 40 ዓመት ነው፡፡
ናቲ፡ እንዴ…. በጣም ረጅም ዓመት የሆናቸው ብዙ አሉ እኮ! ከ 10 እስከ 20 ዓመት በላይ አብረው የዘለቁ…እስካሁንም አብረው ያሉ አሉ፡፡ ያው… ብዙም አናውቃቸውም እንጂ…. እንሰማለን፡፡ በተለይ በተለይ ሴቶች ብዙ አሉ፡፡
ጥያቄ፡ እኔም አለሁ…ይኸው ከራሴ ጋር ሪሌሽንሺፕ ውስጥ ከገባሁ… 5 ዓመታት አልፈውኛል፡፡
ናቲ፡ ሃሃሃሃሃሃሃ
ጥያቄ፡ ግን ደግሞ በአብዛኛው ዜጋ ማህበረሰብ ዘንድ “ዜጋ ለሪሌሽንሺፕ አይሆንም…. ቢሆንም ከ3 ወር በላይ አይዘልም” የሚባል አባባል አለ፡፡ በተወሰነ ደረጃም ዕውነትነት አለው፡፡ እንደየትርጓሜው ቢለያይም፡፡ ለምን ይመስልሃል ዕድሜው የሚያጥረው?
ናቲ፡ ለሰው ብለን እንጂ ለራሳችን ብለን ስለማንጀምረው ይመስለኛል፡፡ ወይም ደግሞ በአንድ ትውውቅ በምናየው ነገር ብቻ ብዙም ሳንተዋወቅ “ካፕል ነን” “ካፕል ነን” ብለን ማውራትም ማመንም እንጀምራለን፡፡ አንድን ሰው ከሴክሹዋሊቲው በዘለለ እውነተኛ ማንነቱን ለማወቅ ስለሚያስቸግረን እና ስለማንፈልግ ይመስለኛል፡፡ እርግጥ ነው ለሱም ብዙ ምክንያቶች አሉት፡፡
እንደገናም እኮ…. ወጥተን በደንብ የምንተዋወቀው … ራሳችንን አውቀን አምነን የምንኖረው እኮ ያን ያህልም ብዙ አይደለንም… እና የምናውቀው የዚህኑ ትንሽ ስብስብ ልምድ ነው፡፡ እንጂ… አሁን ያወራናቸው የሪሌሽንሺፕ ችግሮች በሙሉ በማንኛውም ሰው ላይ… ቀጦች ላይ እንዲያውም ቢብስ እንጂ… የሚኖር የማህበራዊ ህይወት አንዲ አካል ነው፡፡ ያው እኛ በደንብ የምናውቀው የራሳችንን ስለሆነ ጎልቶ ይታየናል እንጂ፡፡ አግብተው ፣ ልጅ ወልደው ቤተሰብ መስርተው የሚወሰልቱ ብዙ ናቸው እኮ… ግን አንዴ በማህበረሰቡ ትክክል ነው በተባለው አካሄድ ተጋብተው ቤተሰብ ስለመሰረቱ ያንን ማፍረስ ሌሎች መዘዞችንም ይዞ ስለሚመጣ ብዙም ሲያደርጉት አይስተዋሉም፡፡ እና ፐርፌክት ይመስለናል – አይደለም፡፡ ያላገቡ ቀጥ ወጣቶችም ቢሆኑ… እነሱም ከ3 ወር በላይ ሪሌሽንሺፕ የላቸውም… አብዛኞቹ፡፡
ጥያቄ፡ በጣም ትክክል ብለሃል፡፡ የኛም የህይወት አካሄድም ይመስለኛል፡፡ ለሁሉም ነገር አዲስ ነን እኮ…. ሴክሹዋሊቲ ምን ማለት እንደሆነ ገና በደንብ ገብቶን አልጨረስንም እኮ…. ከራሳችን ጋር ያለን ትግል አለ… ከዛ ደግሞ ከሰዎች ጋር የምናደርገው ትግል አለ…. ማንነቴ ትክክል አይደለም የምትል ትንሽ ጥርጣሬ እንኳን…. በሰው ላይ አይደለም በራስህ ላይ ሙሉ በሙሉ ዕምነት እንዲኖርህ አታደርግህም፡፡ እና…. አልፈርድም ለማለት ነው፡፡
ናቲ፡ ስለዘህ… ንቃቱ ያለው … የተሻለ የሪሌሽንሺፕ ልምድ እና ታሪክ ያላቸው … በራሳቸው ዕምነት ያላቸው ዜጋ ካፕሎች ያስፈልጉናል ፣ ልምዳቸውን ሊያጋሩን ይገባል ፣ ከህይወታቸው ልንማር ይገባል፡፡ ሌሎቻችንም … እርስ በርሳችን በሰውነት ደረጃ ልንተዋወቅ ልንግባባ ይገባል፡፡ ሴክሹዋሊቲአችን እኮ አንዱ የህይወታችን አካል ነው እንጂ… እኛነታችንን የሚወስን ነገር አይደለም፡፡ ናቲን ናቲ ያደረጉት በጣም ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ዜጋ መሆናችን አንድ ስላደረገን ብቻ ካገኘነው ሰው ጋር ሁሉ የፍቅር ግንኙነት ይኖረናል ማለት አይደለም፡፡
ጥያቄ፡ በጣም ትክክል!
እሺ ናቲሻ…. እስከ 3ኛ አንቃረርን…. ወሬአችን ግን የሚያልቅ አይመስልም፡፡ ለዛሬ በዚህ ይብቃን… ሌላ ጊዜ ደግሞ ተገናኝተን ስለ ሌሎች ነገሮች እንደምናወራ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ስለነበረን ቆይታ እጅግ በጣም አመሰግናለሁ!
ናቲ፡ እኔም በጣም አመሰግናለሁ፡፡ አሪፍ ነገር ነውና የጀመርከው በርታ!
© የዜግነት ክብር – ከዶሚነስ ጋር 2012 ዓ.ም