የተመሳሳይ ፆታ ተማርኮ በኢትዮጵያ ስነ-ፅሁፍ ውስጥ

እ.አ.አ በ ኦክቶበር 05 2013 አዲስ አድማስ ጋዜጣ በጥበብ ዓምዱ በአምደኛው ወልደመድህን  ብርሃነመስቀል ፀሐፊነት “የአማርኛ ልቦለዶችና የግብረሰዶም ባህሪ ማቆጥቆጥ” በሚል ርዕስ አንድ ዘገባ አውጥቶ ነበር፡፡ ፅሁፉ ለአንድ የግል ኮሌጅ የመመረቂያ የተዘጋጀ ጥናትን ተመርኩዞ እንዴት የተለያዩ የተመሳሳይ ፆታ ፍቅርን የሚያትቱ ታሪኮች በተለያዩ ኢትዮጵያዊ የሆኑ እና በኢትዮጵያውያን የተፃፉ ልብ ወለዶች ውስጥ እንደተካተቱ ያስታውሳል፡፡

በተለይም በ1963 የተፃፈው የኃይለ ሥላሴ ደስታ “የሚያቃጥል ፍቅር”  ፣ የ1952ቱ የታደሰ ሊበን “ሌላው መንገድ” እንዲሁም የስብሐት ገብረእግዚአብሔር  “ማስታወሻ” (በደራሲ ዘነበ ወላ የተዘጋጀ) የተባሉ ልብወለድ ስራዎች በአገራችን የተመሳሳይ ፆታ ፍቅር እንደ አሁኑ በደንብ አይታወቅ እንጂ ከግማሽ ክ/ዘመን በፊት ይተረክ እንደነበር የሚጠቁሙ ናቸው፡፡  


“የአማርኛ አጭር ልቦለድ ጀማሪ ተብለው ከሚጠቀሱት ደራስያን አንዱ የሆነው ታደሰ ሊበን በ1949 ዓ.ም “መስከረም”፣ በ1952 ዓ.ም “ሌላው መንገድ” የተሰኙ ሁለት የአጫጭር ልቦለድ መድበሎች ያሳተመ ሲሆን ደራሲው በኢትዮጵያ ውስጥ የግብረ ሰዶማውያንን ሁኔታ የሚያመለክት ጭብጥ በማንሳት ፈር ቀዳጅ እንደሆነ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር በ2000 ዓ.ም ያሳተመው ደራሲያንን የሚያስተዋውቅ አውደ እለት (አጀንዳ) ይጠቁማል፡፡
“ሌላው መንገድ” ስድስት አጫጭር ልቦለድ ታሪኮችን ያካተተ ሲሆን፤ በመጽሐፉ ከገጽ 55 እከ 74 የሚዘልቀው ታሪክ ዋና ገፀባሕሪ፣ ብርሃኑ የሚባል የ22 ዓመት ወጣት ነው፡፡ ታሪኩን “እኔ” እያለ በአንደኛ መደብ የሚተርከው ገፀባህሪ፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደንበኞች ቼክ ክፍል ውስጥ ነው የሚሰራው፡፡
ከቁመቴ ማጠር በስተቀር ደም ግባቴ በጣም ቆንጆ ነበር፡፡ ይህንንም በየዕለቱ የተለያዩ ሰዎች በተለይ ሴቶች የሚያረጋግጡልኝ እውነት ነበር የሚለው ብርሃኑ፤ መልከመልካምነቱን ሲገልፅ፤ “ቀጥ ያለ አፍንጫ፣ ትክክል የሆኑና ንጣታቸው በረዶ የመሰሉ ጥርሶች፣ እጅግም ያልወፈሩ እጅግ በጣም ያልሳሱ መካከለኛ ከንፈሮች፣ ቅንድቦቼ የተኳሉና የተቀነደቡ የሚመስሉ፣ ፀጉሬ፣ ግንባሬ፣ ጉንጮቼ፣ ጆሮዎቼ፣ እምንም ዘንድ ያልተዛቡ፤ በጠቅላላው የሰራኝን እጅ ረቂቅነት አጉልተው የሚያወሱ ነበሩ። ለሴቶችም የማይችሉት ፈተና ነበርኩ…ሲያዩኝ መተርከክ፣ ማተኮር፣ መገላመጥ ግዴታቸው ነበር፡፡”
ጥሩ መልበስ ውበቴን ስለሚያጐላው አልባሌ ነገር መልበስ አዘወትር ነበር የሚለው ዋና ገፀ ባሕሪ፤ በ1942 ዓ.ም እለተ ሰኞ የገጠመውን ይተርካል። በቼክ ክፍል ለመገልገል የመጡ አንድ ደንበኛው ካስተናገዳቸው በኋላ፣ ለአንድ ጉዳይ እንደሚፈልጉት በመግለፅ እቤታቸው እንዲመጣ ይቀጥሩታል፡፡
ሰውየው በትልቅ ቪላ ቤት ውስጥ ነዋሪ ናቸው፡፡ የግቢ ጠባቂ ዘበኛ፣ የእልፍኝ አስከልካይ ወንድና ሴት አገልጋዮችም አሏቸው፡፡ መኖሪያ ቤታቸው ዘመናዊና በውድ ዕቃዎች የተሞላ ነው። ቀጠሮ የሰጡት ወጣት ሲመጣ፣ ውስኪ እየጋበዙ ያጫውቱት ጀመር። የእጅ ሰዓት ከኤደን (የመን) እንደሚያመጡለት ቃል ገቡለት፡፡ ሁለት ሙሉ ልብስ የሚያሰፋበትን ጨርቅ በአቅራቢያው ካለው ሱቅ እንዲወስድም ነገሩት፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ጉዱ የመጣው፡፡ “ሁሉ ሰው፣ መቼም ተፈጥሮ ሆኖ አንዳንድ አመል አለው” በማለት ፍላጐታቸውን በግልጽ ነገሩት፡፡
በቀረበለት ጥያቄ ግራ የተጋባው ብርሃኑ፤ “ምንም አልመለስኩለትም፤ ብቻ… አመዴ ቡን ብሎ ኩምሽሽ አልኩኝ” ይላል – የገጠመውን ሲተርክ። ከዚያም በብልሃት ከሰውየው ወጥመድ አምልጦ መውጣቱን ይተርካል፡፡
ነገሩ ከተከሰተ ከስድስት ወር በኋላም ሰውየው ተመሳሳይ ጥያቄ ለጓደኛው እንዳቀረቡለት ነግሮን ነው ታሪኩ የሚጠናቀቀው፡፡”
የአማርኛ ልቦለዶችና የግብረሰዶም ባህሪ ማቆጥቆጥ
Written by  ወልደመድህን ብርሃነመስቀል
አዲስ አድማስ – ኦክቶበር 05 2013

አዲስ አድማስ ይዞት የወጣው ዘገባ የተመሳሳይ ፆታ ፍቅርን እንደ “ከውጭ አገራት የመጣ አፈንጋጭ ልማድ” አድርጎ ቢስለውም እነዚህ ደራስያን በተለይም ኃይለሥላሴ ደስታ “በሕብረተሰቡ ውስጥ ካየውና ከሰማው በመነሳት” ይሔንን መፅሐፍ እንደፃፈው ይናገራል፡፡

ይህን ዘገባ ዛሬ ላይ ሆኜ ሳነበው ፣ በልጅነቴ ያደግሁበት አካባቢ ይኖር የነበረ አንድ ሰው ትዝ አለኝ፡፡ ይህ ሰው በአካባቢው ሰዎች ዘንድ በሥነምግባሩ እና በማህበራዊ ሕይወቱ ተቀባይነት የነበረውና ተወዳጅ የነበረ ሰው ነበር፡፡ ከጎረቤቶቹ ጋር መልካም ቅርርብ ያለው ፣ ሰርግ ወይም ለቅሶ ሲኖር በጉልበትም ሆነ በሀሳብ ለማገዝ ቀድሞ የሚገኝ ፣ ከቤተክርስቲያን የማይጠፋ ፣ ትልቁንም ትንሹንም በትህትና የሚቀርብ … በሁሉ የሚወደድ ነበር፡፡ ከአንድ ነገር በቀር፡፡ ከጀርባው ከሚወራበት “የግብረሰዶም” ባህሪው፡፡

የአካባቢው ሰው በዚህ ሰው መልካምነት ተገዝቶ አያግልለው እና አይጥላው እንጂ ፣ ከጀርባው ግን በ”ግብረሰዶምነት” ይታማ ነበር፡፡ ሚስት አለማግባቱን እና ልጅ አለመውለዱን ተከትሎ ሽማግሌዎች ትዳር እንዲይዝ ቢወተውቱት እና የተለያዩ ሴቶችን ለሚስትነት ቢያስተዋውቁትም እርሱ ግን በላጤነት ኑሮውን መግፋቱ ሰዎቹን ስለ እሱ የበለጠ ለማወቅ እንዳነሳሳቸው አስታውሳለሁ፡፡ እርሱን ለመቅረብ ፣ ግላዊ ህይወቱን ለማወቅ እና ምስጢራዊ እሱነቱ አነሳስቷቸው ራሳቸውን አሳልፈው ወደሱ የተሳቡ ብዙ የሰፈር ሴቶች ነበሩ፡፡ ሁሉንም ግን ባዶ እጃቸውን ነበር የመለሳቸው፡፡ ይህ ተደጋጋሚ የሴቶቹ ሙከራ እና የአንዳንድ ታላላቆች ጥርጣሬም ነበር የእርሱን “ግብረሰዶማዊነት” ሐሜት ያስነሳው፡፡ ከዛም በኋላ ቢሆን ግን ከጀርባው ከማውራት ባለፈ ፣ ማንም አግልሎት ወይም በግልፅ ተናግሮት አያውቅም ነበር፡፡

የተመሳሳይ ፆታ ተማርኮ ያላቸው ሰዎች የሕብረተሰቡ አካል ናቸው ፤ ነበሩ ፤ ወደፊትም መሆናቸውን ይቀጥላሉ፡፡ በባህል እና በኃይማኖት ምክንያት የሆነ ጊዜ ላይ ተሸሽገው ፣ ራሳቸውን ደብቀው ወይም እንዲደብቁ ተገድደው ሊቆዩ ይችሉ ይሆናል እንጂ፡፡ ምንም ያህል ብንሸፋፍነው እና ባዕዳዊ አንድምታ ብናላብሰውም እነዚህ ቀደምት የስነፅሁፍ ስራዎችም ማረጋገጫዎች ናቸው፡፡

አሁንም ይህ ዘገባ ከጠቀሳቸው መፃሕፍቶች ውስጥ የ1952ቱ የታደሰ ሊበን “ሌላው መንገድ” መፅሐፍን የማንበብ ዕድሉ ገጥሞኝ ነበር፡፡ በተለይም ይህ ዘገባ ያጠነጠነበት ከገፅ 55 እስከ 74 ያለው “አንድ አጋጣሚ” የሚለው ታሪክም ፣ ለጓደኛዬ (ስማቸውን አልጠቅሰውም) ምሥጋና ይግባና እጄ ላይ ይገኛል፡፡

ይህንኑ ታሪክ እንደወረደ ገልብጬ እስካጋራችሁ ድረስ ፣ እስከዛው ይህንን ሊንክ በመጫን የአዲስ አድማስን ዘገባ እያነበባችሁ ጠብቁኝ፡፡
ምንጭhttps://www.addisadmassnews.com/index.php?option=com_k2&view=item&id=13041:%E1%8B%A8%E1%8A%A0%E1%88%9B%E1%88%AD%E1%8A%9B-%E1%88%8D%E1%89%A6%E1%88%88%E1%8B%B6%E1%89%BD%E1%8A%93-%E1%8B%A8%E1%8C%8D%E1%89%A5%E1%88%A8%E1%88%B0%E1%8B%B6%E1%88%9D-%E1%89%A3%E1%88%85%E1%88%AA-%E1%88%9B%E1%89%86%E1%8C%A5%E1%89%86%E1%8C%A5&Itemid=211