የተመሳሳይ ፆታ ፍቅር እና አፍሪካ

የተመሳሳይ ፆታ ፍቅር ወይም የፍቅር ግንኙነት ለአፍሪካ እንግዳ ነገር ሆኖ አያውቅም፡፡ ነጮች ወደ አፍሪካ ከመምጣታቸው በፊት እና ከ ቅኝ ግዛትም በፊት ነበረ፡፡ ታዋቂ የታሪክ ምሁራን ያካሄዷቸው ጥናቶች ፣ በተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ድርጅቶች እንዲሁም (በተለይም) በኡጋንዳው ሴክሹዋል ማይኖሪቲስ ኡጋንዳ (Sexual Minorities Uganda – SMUG) የወጡ ዘገባዎች ግብሩ/ ግንኙነቱ ከምዕራባውያኑ የተገኘ ወይም የተወረሰ ሳይሆን ፣ እንዲያውም ምዕራባውያኑ አፍሪካን ከፋፍለው ከመቀራመታቸው በፊት ይገኝ እንደነበር ያወሳሉ፡፡

ኬንያዊው የታሪክ መምህር እንዳሉት “የተመሳሳይ ፆታ የፍቅር ግንኙነት ቅኝ ገዢዎች ወደ አፍሪካ ከመምጣታቸው በፊት ለረጅም ጊዜ ይገኝ እና ይተገበር ነበር፡፡”

ዓለም አቀፍ ተቃውሞን ችላ በማለት በፕሬዚዳንቷ ፊት አውራሪነት አወዛጋቢውን ፀረ-ተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ህግ ባወጣችው ኡጋንዳ ፣ አብዛኛው ህዝቧ በተሳሳተ ሁኔታ የተመሳሳይ ፆታ ፍቅር በምዕራባውያን በተለይም በአሜሪካ የሚደገፍ እና የሚተዋወቅ ከመሆን በዘለለ ፣ በቅኝ ግዛት ጊዜ ነጮች ያስተዋወቁት ተግባር እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ሙሉ በሙሉ ስህተት ቢሆንም፡፡

በጣም ታዋቂ ከሆኑ አፍሪካውያን የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች መካከል በወቅቱ በምሥራቅ አፍሪካ በጣም የተደራጀ መንግሥት ንጉሥ  የነበሩት የዛኔዋ ቡገንዳ የአሁኗ ኡጋንዳ ንጉስ ዳግማዊ ማዋንጋ (King Mwanga II) ይገኙበታል፡፡

ከ 1884 እስከ 1888 (እ.ኤ.አ) ነግሶ የነበረው ይህ የቀድሞ የኡጋንዳ ንጉስ ከወንድ ባለሟሎቹ ጋር የፍቅር እንዲሁም የወሲብ ግንኙነት እንደነበረው በሰፊው ይነገራል፡፡ ኡጋንዳ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር የወደቀችው በ1894 መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

የጥናት ባለሞያው አምብሮስ ሙካሳ እንዲህ ብሏል፡ “ንጉስ ዳግማዊ ምዋንጋ ብዙ ወጣት ወንዶች በቤተ መንግስቱ ይኖሩ እንደነበር ፣ ለወሲባዊ ግንኙነትም ያገለግሉት እንደነበር መረጃዎች አሉ፡፡ ሚስዮናውያን ክርስትናን በሚያስተዋውቁበት ጊዜ ግን አንዳንዶቹ ወጣቶች ተጠምቀው ፣ እንዲሁም የተመሳሳይ ፆታ ወሲባዊ ግንኙነትን አስከፊነት በመማራቸው ፣ ንጉስ ምዋንጋ ከነሱ የሚያገኘውን ወሲባዊ ጥቅም መከልከል ጀመሩ፡፡”

ንጉስ ምዋንጋም ወጣት ቅምጦቹ ትዕዛዙን በመጣሳቸው ፣ እንዲሁም እንደ በፊቱ ለሱ መታዘዝ እምቢ በማለታቸው ተበሳጭቶ ከሚስዮናውያኑ ጋር ግጭት ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡ አልታዘዝ ያሉትንም እንዲገደሉ ትዕዛዝ አስተላለፈ፡፡ ከ1885 እስከ 1887 ድረስም የተቃወሙትን ሁሉ አስገድሎ ነበር፡፡ የተገደሉትም ወጣቶች ለንጉሳቸው ከመገዛት ይልቅ ለአዲሱ ኃይማኖታቸው ራሳቸውን አሳልፈው ስለሰጡ የ”ሰማዕት”ነት ማዕረግ ተሰጥቷቸው ነበር፡፡

ንጉስ ዳግማዊ ምዋንጋ

በቡጋንዳ ግዛት “ባፌ” (Bbaffe ) ማለት “ባላችን/ባለቤታችን” ማለት ነው፡፡ በንጉስ ምዋንጋ ስር የነበሩ ሰዎች በሙሉ ፣ ወንዶቹን ጨምሮ ንጉሱን “ባፌ” (Bbaffe) በማለት እንዲጠሩት ታዘው ነበር፡፡ ወንዶችንም አግብቶ ይኖር ነበረና፡፡

“ወንዶች እንኳን ንጉስ ምዋንጋን “ባፌ” ብለው ይጠሩት ነበር፡፡ ያ ማለትም በፈለገው ጊዜ የግብረ ስጋ ግንኙነት ከነርሱ ጋር የማድረግ ሙሉ ነፃነት ነበረው ማለት ነው፡፡ ለሁሉም ወንዶች እንዲሁም ሴቶች እንደ ባል ነበረ፡፡” – የቡጋንዳ ትልቅ ሰው ሲሞ ሙጌሬ እንደተናገሩት፡፡

SMUG በዘገባቸው፡  የወቅቱ የኡጋንዳ ፕሬዚዳንት ሙሴቬኒ በአፍሪካዊ ባህሎች ውስጥ የተመሳሳይ ፆታ ፍቅር ግንኙነቶች ይገኙ እንደነበር ያመኑበትን ንግግራቸውንም ጠቅሷል፡፡ “በማህበረሰባችን ውስጥ ጥቂት የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ነበሩ፡፡ አይፈረድባቸውም ፣ አይገደሉም እንዲሁም አይገለሉም ነበር፡፡” ብለዋል፡፡

ይህም የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ከቅኝ ግዛት በፊት በነበረችው አፍሪካ ስለመገኘቱ ብቸኛው ማስረጃ አይደለም፡፡ በ 1606 (እ.ኤ.አ) በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ይንቀሳቀስ የነበረ የ”ኢየሱስ አማኞች ህብረት” (የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን) ቄስ እንደገለፀው “ቺባዲ (chibiadi)”  የተባሉ እንደ ሴቶች የሚለብሱ ፣ እንደ ሴቶች የሚንቀሳቀሱ ወንዶች እና ወንዶች ተብለው መጠራታቸው የሚያሳፍራቸው እና የሚያስቆጣቸው ሰዎች እንደነበሩ ይገልጣል፡፡

በ17ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢም በአሁኗ አንጎላ ይንቀሳቀሱ የነበሩ ፣ ጋስፓር አዝቬሬዱች እና አንቶንዮስ ሴኩዬሬስ (Gaspar Azevereduc and Antonius Sequerius ) የተባሉ ቄሶች ፣ እንደ ሴት የሚያወሩ ፣ እንደ ሴት የሚቀመጡ እና እንደ ሴት የሚለብሱ እንዲሁም ከሌሎች ወንዶች ጋር በጋብቻ የሚጣመሩ ወንዶች አጋጥመዋቸው እንደነበረ ይናገራሉ፡፡ እነዚህ ጋብቻዎች ከመከበራቸውም ባለፈ ይሸለሙ እንደነበር ያወሳሉ፡፡

እንደ የ90 ዓመቱ የኬንያ ቴሶ (Teso) ማህበረሰብ አዛውንት ኤጃካይት ኤሞሮት (Ejakayit Emorot) ታሪካዊ መረጃ ደግሞ ፣ እንደ ሴት በሚንቀሳቀሱ ፣ በማህበረሰቡ ውስጥ ተቀባይነት ባላቸው ሰዎች መሃል የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት እንደነበር ይናገራል፡፡

ከቅኝ ግዛት በፊት በነበረችው ቤኒን ደግሞ የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ወጣት ወንዶች ከሚያልፉባቸው የዕድገት ደረጃዎች ወይም ባህሪያት ውስጥ እንደ አንዱ ይቆጠር ነበር፡፡

በአሁኖቹ ጋቦን እና ካሜሩን የሚገኙ የባንቱ ቋንቋ ተናጋሪ ፖሄይን (Pouhain ) ገበሬዎች ዘንድም የተመሳሳይ ፆታ የፍትወት ግንኙነት ‘bian nkuma’ (ቢያን ንኩማ) በመባል ይታወቅ ነበር፡፡ ይህም በወንዶች መካል የሚደረገው ፍትወታዊ የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ከአንዱ ወደ አንዱ እንደሚተላለፍ የሀብት መድኃኒትነት ይቆጠር ነበር፡፡

እነዚህ ምሳሌዎች እና ብዙ ሌሎችም በብዙ አፍሪካዊ ማህበረሰቦች ዘንድ መገኘታቸው የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ቅኝ ገዢዎች ወደ አፍሪካ ከመምጣታቸው በፊት ለረጅም ጊዜ አፍሪካ ውስጥ ይገኝ/ይተገበር እንደነበር ያረጋግጣሉ፡፡

የተመሳሳይ ፆታ ፍቅር ወይም ግንኙነት “አፍሪካዊ አይደለም” የሚለው ሀሳብ ግን ብዙም በመረጃ የተደገፈ አይመስልም፡፡

አንድ ነገር ግን ግልፅ ነው፡ ዛሬ ላይ የተመሳሳይ ፆታ ፍቅር ህገወጥ በሆነባቸው የአፍሪካ ሀገራት በአብዛኞቹ ፣ ህጉ የተዋወቀው እና የተተገበረው በቅን ገዢዎች መሆኑ፡፡

ሰናይ ቀን!

ምንጭ ፡ https://www.gaystarnews.com/article/africas-lgbti-history-randy-kings-gay-sex-medicine200214/