ማንነቴን ለምን እጠላለሁ?
ያደግነው ፣ የኖርነው ማህበረሰባዊ እና ሕብረተሰባዊ ባህሎችን ፣ ዕሴቶችን እና ሁኔታዎችን እየተማርን ነው፡፡ በዚህ በምናውቀው የተመሳሳይ ፆታ ፍቅር ጠል ፣ አባታዊ ስርዓት ተኮር እና ፆታዊ መድልዎ በተንሰራፋበት ባህል ስለ ተመሳሳይ ፆታ ፍቅር እና ማህበረሰቡ ከለመደው ወጣ ያሉ ፆታዊ ዝንባሌዎች የተሳሳቱ ግንዛቤዎችን ልንሰማና ልንማር እንችላለን፡፡ በዚህም ምክንያት እኛ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያንም ሆንን የፆታ ዝንባሌአችን ከተለመደው የተለየ ሰዎች ልክ እንደማንኛውም የሕብረተሰቡ አባል ከተቃራኒ ፆታዊ ዝንባሌ የተለየ ማንነታችንን እንደ “ልክፍት” ፣ “ስህተት” ፣ “ኃጢአት “ ፣ ወይም ደግሞ “ሥነ-ምግባር የጎደለው” ነገር አድርገን ልናየው እንችላለን፡፡ ይህም ራስን ወደመጠየፍ ወይም ወደመጥላት ስሜት ይመራናል፡፡ እነዚህ ስሜቶች ደግሞ ከፍ ወዳለ ማንነትን የመጥላት “ውስጣዊ ጥላቻ/
የዜግነት ውስጣዊ የማንነት ጥላቻ ምንድን ነው?
ውስጣዊ የማንነት ጥላቻ ወይም ጭቆና ብዙ ጊዜ የሚያጋጥው የተቃራኒ ፆታ ፍቅር ብቻ ትክክለኛው እና “ብቸኛው ፆታዊ ተማርኮ” እንደሆነ እየተማሩ እና እንዲያምኑ እየተገደዱ ባደጉት እና በሚኖሩት የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ፣ እና ሌሎችም ከልማዱ የተለዩ ስብዕናዎች ያሏቸው ሰዎች ላይ ነው፡፡ አንዳንዴም የተቃራኒ ፆታ ተማርኮ ያላቸው ሰዎች ዘንድም ይስተዋላል፡፡ የተለያዩ ዜግነትን እና ዜጎችን በጥላቻ እና በመጥፎ የሚፈርጁ የተሳሳቱ መልዕክቶችን እና ትምህርቶችን እየሰሙ እና እየተማሩ ማደግ ይኼንን የተሳሳተ አመለካከት ወደራስ በመውሰድ ፣ ራስን ወደመጥላት ደረጃ ሊያደርስ ይችላል፡፡ በዚህም ምክንያት ብዙ የዜጋ አባላት ከዚህ ጋር ተያይዞ በሚመጣ ራስን እና ማንነትን የመጥላት ፣ የሚመስለንን የመጥላት የአዕምሮ ጭንቀት ውስጥ እንዘፈቃለን፡፡
አጠቃላይ ለማንነታችን ያለን መልካም አመለካከት ወይም ግምት እና ለግል ወሲባዊ ዝንባሌእን አዎንታዊ አመለካከት መኖር ለአዕምሮአዊ ጤናችን ወሳኝ ናቸው፡፡ አብዛኞቻችን ፣ ምናልባትም ሁላችንም በሚባል ሁኔታ ልክ እንደ አንድ ሌላ ዜጋ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ወይም ምክንያት ዜግነታችንን ከሌሎች ፣ አልፎም ከራሳችን የደበቅንበት ጊዜ ርዝመቱ ቢለያይም ነበረ ፤ አሁንም አለ፡፡
በተለይም የተለመዱ ከሚባሉት እንደ የወንድ ወይም የሴት የተመሳሳይ ፆታ ወሲባዊ ዝንባሌ (ጌይ ፣ ሌዝቢያን) ፣ ወይም የሁለቱም ፆታዎች ወሲባዊ ዝንባሌ (ባይሴክሹዋል) ካሉት ፆታዊ ዝንባሌዎች በዘለለ የሌሎች ተመሳሳይ ማንነቶች ግንዛቤ መጨመር እና እየተገለጡ መምጣት ፣ ቀድሞውኑ የነበረንን ራሳችንን እና ማንነታችንን ያለመፍቀድ ስሜት በተለያዩ ባህሪያት በመገለጥ ፣ ሌላውን ዜጋ ወደማጥቃት ደረጃ ሊያደርሰን ይችላል፡፡
ራስን እና ማንነትን የመጥላት ባህሪይ በተለያዩ ከአዕምሮአዊ ጤና ጋር ተያያዥ በሆኑ መንገዶች ሊገለጥ ይችላል፡
- ፆታዊ ተማርኮን ከራስም ከሌሎችም መደበቅ ብሎም መካድ
- ፆታዊ ተማርኮን እና ማንነትን ለመለወጥ ወይም ለመቀየር መሞከር
- ምሉዕ እና በቂ የአለመሆን ስሜት መሰማት
- ሌሎች እንዲቀበሉን ከመጠን በላይ የሆነ ወይም ምንም ተነሳሽነት ማሳየት
- ለራስ ያለ ዝቅተኛ ግምት ፣ የገዛ ሰውነትን (አካልን) መጥላት
- ሌሎች ማንነታቸውን ተቀብለው ለሚኖሩ ዜጎች የሚታይ እና ግልፅ የሆነ ንቀት
- ሌሎች ማንነታቸውን ለመቀበል በብዙ ችግር ውስጥ ለማያልፉ ዜጎች ያለ ንቀት
- የተመሳሳይ ፆታ ፍቅር ጥላቻ (homophobia) ፣ የተቃራኒ ፆታ ብቻ! ነት (heterosexism) ፣ የፆታዊ ማንነቶች ጥላቻ (Trans and Gender Non-Conforming phobia) ፣ ብሎም ፆታዊ አድልዎ (sexism ) እና ሌሎችም ችግሮች ትኩረት የሚሹ የህብረተሰቡ ችግሮች እንደሆነ አለማመን
- ለሌሎች እኛን ለማይመስሉን ፣ ወይም/እና ለሚመስሉን ያለ ንቀትና ጥላቻ ፣ አልፎ ተርፎም በሌሎች ዜጎችን በመጥላት በሚደረጉ ነገሮች እና ንግግሮች ላይ መሳተፍ
- በሌሎች የሚጠቁ ተጠቂዎች ላይ የበላይነትን ማሳየት
- ጤነኛ ያልሆነ የፍቅር ግንኙነት ውስጥ መቆየት
- ቀጥ ወይም የተቃራኒ ፆታ አፍቃሪ መስሎ ለመታየት መሞከር ፣ አንዳንዴም ለሰዎች ስንል የተቃራኒ ፆታ ፍቅር እና ትዳር ውስጥ መግባት ፣ ወይም “ፈውስን” መመኘት
- ጓደኞቻችን ወይም ዘመዶቻችን እንዳይርቁን ክፉኛ መፍራት
- እፍረት ፣ ድብርት ፣ ንዴት ፣ ነጭናጫነት ፣ ድንጉጥ ፣ አላስፈላጊ የሆነ ራስን የመከላከል ስሜት ፣
- በትምህርት መዳከም ፣ ወይም ማቋረጥ ፤ በሥራ ቦታ ውጤታማነት ማነስ
- ሁልጊዜ የራስ ባህሪይን ፣ ሥርዓተኝነትን ፣ ዕምነትን ፣ አመለካከትን እና ዕይታን መቆጣጠር
- ለዜጎች መብት አቀንቃኞች ያለ አሉታዊ አመለካከት እና ነቀፌታ
- ህፃናት ደፋሪ ላለመባል ወይም ላለመምሰል ከሚመነጭ ውስጣዊ ፍርሃት ህፃናት አካባቢ ላለመሆን መፈለግ
- ደህንነቱ ያልተጠበቀ ወሲብ ማዘውተር ፣ እና ሌሎች ለኤች አይቪ እና ሌሎች የአባላዘር በሽታዎች ተጋላጭ የሚያደርጉ ባህሪያትን ማሳየት
- ፍቅርን እና ወሲብን ከፆታ ጋር በማያያዝ አራርቆ የማየት ባህሪይ ፣ ስሜታዊ ቅርርብን ወይም ፍቅርን መፍራት ፣ አንዳንዴም ዝቅተኛ የሆነ የወሲብ ስሜት
- አደንዛዥ ዕፅ አብዝቶ መጠቀም ፣ መጠጥንን እና መድኃኒቶችን ጨምሮ
- ራስን ስለማጥፋት ደጋግሞ ማሰብ ፣ መሞከር ፣ እናም ራስን ማጥፋት
- ሌሎችም…..
እኒህን እና ሌሎችም የመሳሰሉ ራስን ዜግነትን የመጥላት እና የመጨቆን አመለካከቶች እና ባህሪይያት የአንድን ሰው አዕምሮአዊ ጤና ከመበረዝ በተረፈ አስተሳሰባችንን ፣ ለሰዎች ያለንን መልካም አመለካከት ፣ ለሌሎች ያለንን ክብር ፣ ስሜቶቻችንን ፣ ዕምነታችንን እና ዕውነተኛ ማንነታችንን የመቀየር እና የመበከል ችግር አለባቸው፡፡
ታዲያ ይኼንን ብዙዎቻችን ፈልገን ያላመጣነውን ፣ ከተማርነው ፣ ካደግንበት ፣ እና ትክክለኛ ብለን ካመንነው የተሳሳተ ባህል እና ዕሳቤ የወረስነውን ችግር በጥንቃቄ ይዘን ካላስታመምነው እና ፣ ዕውነታዎችን እና ነባራዊ ሁኔታዎችን እያጣቀስን ፣ ተሸሽገውብን የኖሩ ዕውነቶችን ፣ ዕውቀቶችን ልንመግበውና ራሳችንን ወደመቀበል በመምጣት ሕይወትን በተሻለ ሁኔታ የምናጣጥምበትን መንገድ ልንፈጥር ይገባል፡፡
- ልክ እኛ የምናልፍበትን ዓይነት ጥያቄና የሕይወት አለመመቸትን ሌሎችም በራሳቸው መንገድ እንደሚያልፉበት መገንዘብ
- ሰዎች አንዳችን ከአንዳችን የተለያየ የማንነት አገላለፅ ፣ ፆታዊ ተማርኮ እንዳለን መረዳት
- ሁላችንም የተለያየ የራሳችን የሆነ ራሳችንን የመቀበል ሂደት እና ጊዜ እንዳለን ማወቅ
- አገላለፁ እኛ ባንረዳው እና ባይገባን እንኳ ሰውን በሰውነቱ ብቻ መቀበል መቻል
- ሁሉም ሰው የተለያየ ራሱን የመከላከያ ፣ ማንነቱን የማሳወቂያ መንገድ እንዳለው መገንዘብ
- ስለ ፆታዊ ተማርኮ እና ማንነት የበለጠ ለማወቅ መትጋት
የተሻለ ማህበረሰባዊ መቻቻልን ለመፍጠር እና በህብረት ለደህንነቱ የሚተጋ እና ሌሎችን በማክበር ዜግነትን በአጠቃላይ ከሚጠላው የህብረተሰብ ክፍል የሚመጣውን ጥላቻ እና ጥቃት ለመከላከል እና ግንዛቤን ለማስጨበጥ የሚተባበር ጤናማ ሕይወት ያለው ዜጋን መፍጠር እንችላለን፡፡
መልካም ምሽት!